Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ መንግስት እና በኦብነግ መካከል የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ የሶማሌ ክልል ህዝብ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ሰላም፣ መረጋጋትና ሁለንተናዊ ዕድገት ማስመዝገብ ችሏል – ኦብነግ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ መንግስት እና በኦብነግ መካከል የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ የሶማሌ ክልል ህዝብ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ሰላም፣ መረጋጋትና ሁለንተናዊ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉን የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጭ ግንባር(ኦብነግ) ገለጸ፡፡

የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጭ ግንባር(ኦብነግ) ያወጣውን ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ይቀርባል፦

ከኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጭ ግንባር(ኦብነግ) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጭ ግንባር(ኦብነግ) በ2018 ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የተደረገው የሠላም ስምምነት ፍሬዎች (ትሩፋቶችን) ይገነዘባል እውቅናም ይሰጣል፡፡

ይህ ስምምነት በህዝባችን ሁለንተናዊ መስተጋብሮች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበረሰባዊ ገፅታዎችን ጨምሮ ያበረከተውን አዎንታዊ አስተዋፅኦም ተመልክተናል፡፡

የ2018ቱ የሰላም ስምምነት በወቅቱ ተከስቶ የነበረው ሀገር አቀፋዊ ለውጥና ለውጡን ተከትሎ የመጣው አመራር ለፖለቲካዊ ግልጸኝነትና ተቋማዊ ለውጦችን ለማምጣት የነበረው ቁርጠኝነት ቀጥተኛ ውጤት ነበር፡፡

በአመራሩ በኩል የነበረው ፖለቲካዊ ግልፅነትና ተቋማዊ ሪፎርሞች ደግሞ የተለያዩ ቡድኖች ህገመንግስታዊ መብቶቻቸው የተከበሩ የመሆናቸው ማረጋገጫ ነበር፡፡

እነኝህን ለውጦች መሠረት በማድረግ ኦብነግ ያደርግ የነበረውን የትጥቅ ትግል በማቆም የፖለቲካ ጥያቄዎቹን ሠላማዊ በሆነ መንገድ ለማስቀጠል መወሰኑን ከሶማሌ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የሰላም ስምምነቱ በኢትዮጵያ መንግስት እና በኦብነግ መካከል ከተፈረመ በኋላ የሶማሌ ክልል ህዝብ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ሰላም፣ መረጋጋትና ሁለንተናዊ ዕድገት ለማስመዝገብ ችሏል፡፡

ኦብነግ ሲታገል የነበረው የሶማሌ ክልል ህዝብ እድል በራሱ መወሰን እንዲችል፣ ፖለቲካ እና ሰብአዊ መብቶች የተከበሩ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ቀደም ሲል በህዝባችን ላይ ሲደርስ የነበረውን ታሪካዊ ኢፍትሃዊነትና የመብት ረገጣ ለማስተካከል ረዘም ያለ ጊዜ እንደሚፈልግ ቢረዳም ከ 2018 በኋላ ራስን በራስ በማስተዳደር ረገድ በሰብአዊ መብት ጥበቃና ክልላዊ እድገት ረገድ ለታዩት አዎንታዊ ለውጦችና መሻሻሎች ግን እውቅና ይሰጣል፡፡

ኦብነግ አሁንም የሶማሌ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ መብቱ ራስን በራስ መምራትን ጨምሮ የተገበሩ እንደሆነ ሰላማዊ የሆነ የትግል አማራጭ ተጠቅሞ ዕሙን ለማድረግ ቁርጠኛ በመሆኑም ከዚህ የፓለቲካ ትግር ስልታችንና አላማችን የማይጣጣሙ መግለጫዎችን ኦብነግ አይቀበልም፡፡

እንደዚህ አይነት መግለጫዎች በፓርቲያችን ውስጥ ባሉ ግለሰቦች የተሰነዘሩና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ውሳኔ ሰጪ አካል ይሁንታ የሌላቸው ባዶ ሀተታዎች መሆናቸውን እየገለፅን እነኝህ ግለሰቦች የፓርቲው ህግጋትና ደንቦች አክብረው የተናጠል መግለጫዎችን እንዳይሰጡና ከፓርቲው ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ጋር ከሚቃረኑ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ እያሳሰብን እንዲህ ያሉ ድርጊቶች ለሶማሌ ህዝብ ሰላም፣ አንድነት፣ መረጋጋትና የኢኮኖሚ ማገገም ስጋት መሆናቸውን ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

አብዲ ከሪም ሼክ ሙሴ
ም/ሊቀመንበር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.