Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ እያሳየች ያለችው የላቀ ውጤትና እመርታ ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ እያሳየች ያለችው የላቀ ውጤትና እመርታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለፀ።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር)ኢትዮጵያ በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ የላቀ ውጤትና እመርታ ያሳየች መሆኑን ገልጸው፤ ይኸው ሥራ በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን ገልፀዋል።

የአየር መንገዱን የሀገር ከፍታ ማሳያና የመልካም ገፅታ መገለጫነት የሚያስቀጥሉ አዳዲስና ዘመናዊ አሠራሮች አሁንም ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለዘመናት የሀገር ኩራትና የኢትዮጵያውያኖች ምልክት ከመሆንም ባለፈ በዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ዘርፍ ግንባር ቀደም ተቋም መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የአየር መንገዱን ስምና ዝና ጠብቆ ስኬታማነቱን ማስቀጠል የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።

የአየር መንገዱ ስኬታማ ጉዞ አሁንም በላቀ መልኩ መቀጠሉን የተናገሩት ዶክተር ዓለሙ(ዶ/ር) በተቃራኒው መልካም ስሙን ለማጠልሸት የሚጥሩ አካላት እንዳሉም ጠቁመዋል።

በአሠራር ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮች ቢኖሩ እንኳን በጥብቅ ዲሲፕሊንና አሠራር የሚስተካከሉ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በአየር መንገዱ ላይ በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚሰነዘሩ አሉባልታዎችና የስም ማጥፋት ዘመቻዎች ግን ከእውነታ የራቁና በፍፁም ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑን ገልፀዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየትኛውም ያልተገባ ዘመቻ ሳይደናገር ከሀገር ኩራትነቱ ባለፈ በዓለም ተመራጭ አየር መንገድነቱ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው÷ አየር መንገዱ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት መንገደኞችን በማጓጓዝ ረገድ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ29 በመቶ፣ በገቢ የ14 በመቶ እንዲሁም ትርፋማነት 22 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ 145 አውሮፕላኖች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው በቅርቡ የአዳዲስ አውሮፕላኖች ግዥ ትዕዛዝ መሰጠቱን ጠቁመዋል።

አየር መንገዱ በአሠራሮች በጥብቅ ዲሲፕሊን የሚመራ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ በአሠራር ሂደት ችግሮች ካጋጠሙ በፍጥነት የሚፈቱና ምላሽም የሚሰጥባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም መንግስቴ÷የአየር መንገዱ ሰላምና ደኅንነት በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ በጥብቅ ዲሲፕሊን እየተጠበቀ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በኤርፖርት ዙሪያ የወንጀል ተግባራት ላይ በሚሳተፉ ሰዎች ላይ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ ሕጋዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው መንግስቴ፤ በኢትዮጵያ የበረራ ድኅንነትን በማስጠበቅ ረገድ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር ባደረጉት የኦዲት ሪፖርት መረጋገጡን ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.