Fana: At a Speed of Life!

መገናኛ ብዙሃን ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ቅድሚያ ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መገናኛ ብዙሃን ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ቅድሚያ ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።

ከተለያዩ የግል መገናኛ ብዙሃን ለተውጣጡ ጋዜጠኞች ለአራት ቀናት ሲሰጥ የቆየው የአቅም ግንባታ ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ እንዳሉት፤ መገናኛ ብዙሃን የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅና ሥርዓት ግንባታ ላይ ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

ሀገራዊ መግባባት ላይ መገናኛ ብዙሃን በሚጠበቀው ደረጃ እየሰሩ እንዳልሆነ ገልጸው፤ ሕዝቡን የሚያቀራርቡ አንድነትን የሚያረጋግጡ ሥራዎች ላይ በማተኮር ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ዘንድ ሚዛናዊ ሆኖ ከመዘገብ ይልቅ ወገኝተኝነት እየተስተዋለ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ይህም ለሰላም እና ሀገር ግንባታ ሳንካ በመሆኑ ሊስተካከል እንደሚገባ አስረድተዋል።

መገናኛ ብዙሃን በስራዎቻቸው ሀገርን ማስቀደም እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

በመድረኩ የውይይት መነሻ ያቀረቡት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ በበኩላቸው፤ መገናኛ ብዙሃን አብሮ የሚያኖርና ትውልድ የሚገነባ ስራ እያከናወኑ ስለመሆናቸው ማረጋገጥ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የባለሙያዎች አቅም ማነስ፣ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ እንዲሁም የግንዛቤ ክፍተቶች መገናኛ ብዙሃን በአግባቡ እንዳይሰሩ ከሚያደርጋቸው ምክንያቶች መካከል እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።

በቀጣይም መገናኛ ብዙሃን የሕግና ሙያዊ ሥነ ምግባር ላይ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ስልጠናዎች መስጠት እንዲሁም ተጠያቂነትን የማስፈን ስራ  መተገበር እንደሚገባ አጽንኦት መስጠታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የስልጠናው ተሳታፊዎች የግል መገናኛ ብዙሃን ገቢ በሚያስገኙ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት ማድረጋቸው በብሔራዊ ጥቅምና ሀገራዊ መግባባት ዙሪያ ትኩረት አድርገው እንዳይሰሩ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

መገናኛ ብዙሃን በተለይ ማህበረሰብን ማስተማርና ማንቃት ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

በአንዳንድ ምንጮች ዘንድ የሚስተዋለው መረጃ ያለመስጠት ችግር መገናኛ ብዙሃን በሚፈለገው ደረጃ እንዳይሰሩ እክል መፍጠሩን ጠቁመዋል።

ማህበራዊ ሚዲያው እየፈጠረ ያለው አሉታዊ ጫናም ቸል ሊባል እንደማይገባም ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.