Fana: At a Speed of Life!

በአውሮፓ በአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ አስከፊ አደጋ እንደሚከሰት ተነገረ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አውሮፓ አደጋዎችን ለመቀነስ አስቸኳይ እርምጃ ካልወሰደች በአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ አስከፊ አደጋ ሊደርስባት እንደሚችል አዲሱ የአውሮፓ ህብረት ትንታኔ አስጠንቅቋል።
 
የአውሮፓ የአካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ ባወጣው የመጀመሪያ ሪፖርቱ አህጉሪቱ ስለተደቀነባት የአየር ንብረት ለውጥ ስጋት የገለፀ ሲሆን በዋነኛነትም በደቡባዊ አውሮፓ የሚገኙ አካባቢዎች ለአደጋ የተጋለጡ መሆናቸውን አስታውቋል።
 
አደጋው የእሳት ቃጠሎ፣ የውሃ እጥረት እና በእርሻ ምርት ላይ የሚደርሰውን ተፅዕኖ የሚያጠቃልል ሲሆን በዝቅተኛው የባህር ዳርቻ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ፣ የአፈር መሸርሸር እና በጨዋማ ውሃ መበረዝ ስጋት እንደሚኖር አስገንዝቧል።
 
ከአደጋዎቹ መካከል ብዙዎቹ ቀደም ሲል ከባድ ደረጃ ላይ የደረሱ በመሆናቸው አስቸኳይ እርምጃ ካልተወሰደ የበለጠ አስከፊ ሊሆኑ እንደሚችሉ ኤጀንሲው ገልጿል።
 
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጀርመን የደረሰው የጎርፍ መጥለቅለቅ እና በስዊድን የተከሰተው የደን ቃጠሎ ሰሜናዊ አውሮፓ ከአሉታዊ ተፅዕኖው ይተርፋል ማለት እንዳልሆነ አመላክቷል።
 
በአውሮፓ በቅርብ ዓመታት ውስጥ የታየው ከፍተኛ ሙቀት፣ ድርቅ፣ ሰደድ እሳት እና ጎርፍ ይበልጥ እየተባባሰ እንደሚሄድ እና ኑሮን ሊያከብድ እንደሚችልም ኤጀንሲው አስጠንቅቋል።
 
በአውሮፓ የደረሱ ከአየር ንብረት ጋር የተያያዙ 36 አደጋዎችን የሚዘረዝረው ሪፖርቱ ከእነዚህ ውስጥ 21 አፋጣኝ እርምጃ እንደሚፈልጉ እና 8ቱ ደግሞ በተለየ ሁኔታ አስቸኳይ መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡
 
በዋነኛነትም ከባህር ዳርቻ እና ከባህር ጋር የተያያዙ ስነ-ምህዳራዊ አደጋዎች በዝርዝሩ መጀመሪያ ተርታ ላይ መቀመጣቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.