Fana: At a Speed of Life!

የሀዋሳ ምርት ጥራትና ሰርተፊኬሽን ከ33 ሺህ ቶን በላይ ቡና የጥራት ደረጃ መለየቱን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የሀዋሳ ምርት ጥራትና ሰርተፊኬሽን ማዕከል የታጠበና ያልታጠበ ቡና ለዓለም ገበያ ለማቅረብ እንዲቻል ከ33 ሺህ ቶን በላይ ቡና በመመርመር ደረጃ ሰጥቶ ለማዕከል ገበያ መላኩን አስታውቋል።

በባለስልጣኑ የሀዋሳ ምርት ጥራትና ሰርተፊኬሽን ማዕከል ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ሲማ እንደገለጹት፤ ማዕከሉ ከኦሮሚያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያና ሲዳማ ክልሎች ለሚመጣ ቡና የጥራት ደረጃ ይሰጣል፡፡

ማዕከሉ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለአዲስ አበባ ኤክስፖርት ማዘጋጃ ኢንዱስትሪ በመላክ ኢንዱስትሪው በተራው ለዓለም ገበያ በማቅረብ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ከማሳደግ ባለፈ ቡናው የአካባቢውን ጣዕም ይዞ ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ ማስቻል ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራትም ከ33 ሺህ 500 ቶን በላይ ለአዲስ አበባ ኤክስፖርት ማዘጋጃ ኢንዱስትሪ የሚቀርብን ያልታጠበና የታጠበ ቡና መርምሮ ደረጃ በመስጠት የእቅዱን 75 በመቶ መፈጸሙን ተናግረዋል።

አፈጻጸሙ በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ የተመዘገበ መሆኑን ጠቅሰው÷ በተለይም ማዕከሉ በጊዜያዊነት ስራ የጀመረበት ቦታ ለአገልግሎቱ ምቹ አለመሆኑን አንስተዋል፡፡

ከማዕከሉ ጋር በተያያዙና በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ለተሰማሩ ከ257 በላይ ሰዎች የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ገልጸዋል፡፡

ማዕከሉ የአገልግሎት ደረጃው ለውጭ ገበያ የሚቀርብን ቡና የመጀመሪያ ምርመራ አድርጎ ወደ ማዕከል መላክ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው÷ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን ቡና መጠን ከፍ ለማድረግ እንደሚሰራ አንስተዋል።

ቡናን ለውጭ ገበያ ማዘጋጃ የመቀየር ዕቅዱን ለማሳካት እንዲያስችለውም በቀጣይ የውጭ ገበያ ማዘጋጃ ኢንዱስትሪን እንደሚተከሉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.