Fana: At a Speed of Life!

የገንዘብ ሚኒስቴር ከጣሊያን ተወካዮች ጋር ምክክር አደረገ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በልማት ትብብር ዋና ዳይሬክተር ስቴፋኖ ጋቲ የተመራ የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ የልዑካን ቡድን የገንዘብ ሚኒስቴርን ጎብኝቷል።
 
የጣሊያን ልማት ትብብር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ስቴፋኖ ጋቲ በጣሊያን ኢንተርፕራይዞች ተወካዮች፣ ከካሳ ዴፖዚቲ ኢ ፕሬስቲቲ እና በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር አጎስቲኖ ፓሌሴ ጋር ተገኝተዋል።
 
የልዑካን ቡድኑን የተቀበሉት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታዎቹ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እና ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው፤ በኢትዮጵያ መንግስት ቅድሚያ ከተሰጣቸው ጉዳዮች ጋር ለተጣጣመ ፈጣን የገንዘብ ድጋፍ ለጣሊያን መንግስት ምስጋና አቅርበዋል።
 
በግብርና ማቀነባበሪያ፣ በኃይል፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ የቡና ምርታማነትን በማሻሻልና የእሴት ሰንሰለቱን በማሳደግ፣ በከተሞች ልማትና የልማት ትብብርን በማስፋፋት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችን ለማፋጠን በቅርበት ለመስራት በጣሊያን በኩል ፍላጎት መኖሩ ልዑካኑ ገልፀዋል።
 
በተጨማሪም ጣሊያን የቡድን 7 ፕሬዚዳንት እንደመሆኗ የአየር ንብረት ክፍያ እና በፈረንጆቹ 2023 መጀመሪያ ላይ በጣሊያን መንግስት ይፋ የተደረገውን “ማቲ ፕላን” ለአፍሪካ ልማት ወደ ሥራ እንዲገባ በማድረግ የኢትዮጵያን የልማት ፍላጎት ለመደገፍ ቃል ገብታለች።
 
በማጠቃለያም ለሁለቱ ሀገራት እና ህዝቦች የጋራ ጥቅም በቅርበት ለመስራት የግንኙነት መስመሮችን ለማጠናከር መስማማታቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.