Fana: At a Speed of Life!

መንግስት ጥያቄ አለኝ ከሚል ኃይል ጋር ውይይት ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነ ገለጸ

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት የትኛውም አይነት ጥያቄ አለኝ ከሚል ኃይል ጋር ውይይት ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሰላም ተቋም ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) ጋር በመተባበር በአማራ ክልል የተከሰተውን ግጭት በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶችን ለመደገፍ ዓላማ ያደረገ የምክክር መድረክ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር)÷ በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ግጭቶች የሀገሪቱን የረጅም ጊዜ ገናና ታሪክ የሚያጠለሹና ገፅታዋን የሚያበላሹ እንዲሁም ዜጎችን የሚጎዱ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም መንግስት የትኛውም አይነት ጥያቄ አለኝ ከሚል ኃይል ጋር ውይይት ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በአማራ፣ ኦሮሚያና ሌሎችም አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችን በሃሳብ የበላይነት መፍትሔ ለመስጠት በቁርጠኝነት እየሰራ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የሰላም ተቋም ዘላቂ ሀገራዊ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው፤ ሌሎችም ለዘላቂ ሰላምና ልማት የድርሻቸውን እንዲወጡ መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ የሰላም ተቋም የቦርድ ሊቀመንበር አምባሳደር ሙሉጌታ ኢተፋ (ዶ/ር)÷ በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት የመንግስትን ጥረት አድንቀው ሌሎችም ይህንኑ መልካም አርአያ ሊደግፉት ይገባል ብለዋል።

በአማራ ክልል የተከሰቱ ግጭቶች እያስከተሉት ያለውን ዘርፈ ብዙ ጉዳት በተመለከተ በመድረኩ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ምክክር እየተደረገባቸው ይገኛል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.