Fana: At a Speed of Life!

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራሮች እና ሠራተኞች ለአቶ ደመቀ መኮንን የክብር ሽኝት አደረጉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራሮች እና ሠራተኞች ለቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ምስጋና እና የክብር ሽኝት አደረጉላቸው፡፡

አቶ ደመቀ በነበራቸው የአመራርነት ዘመን ላበረከቱት ጉልህ አስተዋጽኦ ነው የምስጋና እና የክብር ሽኝት የተደረገላቸው፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የአቶ ደመቀ የካበተ የአመራርነት ልምድ ከተቋም ባለፈ በሀገር ደረጃ ወደፊትም ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው ብለዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ጊዜያቸው በተቋሙ የጀመሯቸው መልካም ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በበኩላቸው÷ አቶ ደመቀ መኮንን በተቋሙ በነበራቸው ቆይታ በተለይም ሀገራችን ገጥመዋት የነበሩ ፈተናዎችን እንድትሻገር ችግር ፈቺ ሐሳቦችን በማፍለቅ እና ቆራጥ አመራር በመስጠት ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ስኬት እንድታስመዘግብ አበርክቷቸው የጎላ ነበር ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

በተለይም በተረጋጋ እና በሰከነ አመራር ሰጭነታቸው ከሁሉም ሠራተኞች ጋር በቅርብ በመሥራት እና ሥራዎችን በመከታተል ወደ ተግባር እንዲቀየር ላደረጉት ጥረትም ሊመሰገኑ ይገባል ነው ያሉት፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን ለተደረገላቸው እውቅና ሠራተኛውን እና አመራሩን አመሠግነው÷ በቀጣይም ተቋሙን፣ ሀገራቸውን እና ሕዝባቸውን በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ እንደሚያግዙ ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.