Fana: At a Speed of Life!

መሬት እናሰጣለን በማለት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ተቀብለዋል የተባሉ የቀድሞ የመዲናዋ ሰራተኞች ጥፋተኛ ተባሉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባዶ መሬት እናሰጣለን በማለት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ሙስና ተቀብለዋል የተባሉ የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኞች በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3 ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ጥፋተኛ ተባሉ።

ተከሳሾቹ 1ኛ የአራዳ ክ/ከ ወረዳ 6 የግንባታ ቁጥጥር ባለሙያ ፍቅረስላሴ ታደለ፣ 2ኛ የቀድሞ የአ/አ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤት ቅሬታ ሰሚ ዳይሬክተር ታምራት እስጢፋኖስን እና 3ኛ በየካ ክ/ከ መሬት አስተዳደር የመብት ፈጠራ ቡድን መሪ የነበሩት ዘውዱ ደገፋ ናቸው።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ጀነራል ተከሳሾቹ ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እና ለ የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 32 (2) የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት በማታለል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

በዚህም ቀርቦባቸው በነበረው ዝርዝር ክስ ላይ እንደተመላከተው፤ 1ኛ ተከሳሽ የዐቃቤ ሕግ ምስክር የሆኑ የግል ተበዳይን በማግኘት እራሱን የከተማ አስተዳድሩ የመሬት አስተዳደር ካቢኒ ነኝ በማለት አሳሳች ፍሬ ነገሮችን በመግለጽ የግል ተበዳይ እንዲያምኑ በማድረግ ግለሰቡን በጥቅምት 2 ቀን 2015 ዓ.ም በአራዳ ክ/ከ ወረዳ 5 ከንቲባ ጽ/ቤት ቅጥር ግቢ በመጥራት ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር በመሆን በየካ ክ/ከ ወረዳ 9 አራራት ሆቴል ጀርባ 5 ሺህ ካሬ ሜትር ባዶ ቦታ እንሰጣለን በማለት አስቀድመው 25 ሚሊዮን ብር ሙስና ገንዘብ ከጠየቁ በኋላ በቅድሚያ ለፕሮጀክት ማሰሪያ 250 ሺህ ብር በቼክ ተቀብለዋል።

በጥቅምት 8 ቀን 2015 ዓ.ም ደግሞ የግል ተበዳዩ የኗሪነት መታወቂያ ኮፒ፣ ፓስፖርት ኮፒ፣ የባንክ ስቴትመንታቸውን ኮፒ ሰነዶችን እንዲሰጧቸው በማድረግ በጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም ሁለት ሚሊዮን ብር በቼክ መቀበላቸውን በክሱ የተመላከተ ሲሆን በዚህ መልኩ ከሁለቱ የግል ተበዳዮች 10 ሚሊዮን 250 ሺህ ብር መቀበላቸው በክሱ ተብራርቷል።

በተጨማሪም 1ኛና 2ኛ ተጠርጣሪ የሜሪዲያን ሆቴል ባለቤት ለሆኑት ግለሰብ በሆቴሉ ስም የተመዘገበ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የመከነ ቢሆንም በይዞታው ላይ ጭማሪ ካሬ ሜትር በማካተት የመከነው ካርታ እንደሚስተካከልላቸው በመግለጽ የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶች የከተማ አስተዳደሩ እንደሆኑ ለግል ተበዳይ ማሳየታቸውን እና ሀሰተኛ ሰነዶቹ በ1ኛ ተከሳሽ መኖሪያ ቤትና 2ኛ ተከሳሽ በሚያሽከረክረው ተሽከርካሪ ውስጥ በብርበራ መገኘቱን ጠቅሶ ዐቃቤ ሕግ ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸው እንደነበር ይታወሳል።

ተከሳሾቹ ክሱ ከደረሳቸው በኋላ የዋስትና መብታቸው እንዲፈቀድላቸው ያቀረቡት ጥያቄ ከተከሰሱበት ድንጋጌ አንጻር የዋስትና መብታቸው ውድቅ ሆኖ በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ተደርጓል።

ከዚህም በኋላ የወንጀል ድርጊቱን አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ የሰነድና የሰው ማስረጃ አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን መርምሮ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ቢሆን በተገቢው በተገቢው መከላከል አመቻላቸው ተገልጾ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን አስተያየት መርምሮ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.