Fana: At a Speed of Life!

ንግድ ባንክ የራሳቸው ያልሆነን ገንዘብ የወሰዱ ግለሰቦች እስከ ቅዳሜ ድረስ እንዲመልሱ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የራሳቸው ያልሆነን ገንዘብ የወሰዱ ወይም ወደተለያየ ሂሳቦች ያስተላለፉ ግለሰቦች እስከ መጪው ቅዳሜ ድረስ በፈቃዳቸው እንዲመልሱ አሳስቧል፡፡

ሰሞኑን ባንኩ ካጋጠመው የሲስተም ችግር ጋር ተያይዞ የራሳቸው ያልሆነ ገንዘብ የወሰዱና ያልተገባ የገንዘብ እንቅስቃሴ ካከናወኑ ግለሰቦች መካከል ብዙዎች የተደረገላቸውን ጥሪ አክብረው ገንዘቡን ወደ ባንኩ ቅርንጫፎች እየቀረቡ እየመለሱ በመሆኑ ከስህተታቸው የመመለስ በጎ ምላሽነቱን እናደንቃለን ብሏል፡፡

ገንዘቡን ተመላሽ ያላደረጉ ግለሰቦችም እስከመጪው ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የባንኩ ቅርንጫፍ በመቅረብ ተመላሽ እንዲያደርጉ የመጨረሻ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ይሁን እንጂ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ገንዘቡን ተመላሽ በማያደርጉ ግለሰቦች ላይ ጠንካራ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ ገልጿል፡፡

ከሕግ አካላት ጋር በመተባበር የግለሰቦችን ሥም ዝርዝር በየቅርንጫፎች እና እንደሁኔታው ግለሰቦቹ ሊታወቁ በሚችሉበት አካባቢ ይፋ በማድረግ ቀጣይ ሕጋዊ እርምጃዎች እንዲቀጥሉ እንደሚደረግም ነው ባንኩ የገለጸው፡፡

በእርምጃው መሰረት ቀርበው የማይመልሱ ከሆነ በሕጋዊ ሂደቱ ተገቢው ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ በድርጊቱ የተጠረጠሩትን ግለሰቦች ፎቶግራፍ እና ዝርዝር ማንነታቸውን የሚገልፁ መረጃዎች በብዙሀን መገናኛ መንገድ ለሕዝብ ይፋ የሚያደርግ መሆኑንም አሳስቧል፡፡

ከእርምጃዎች ጎን ለጎንም ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ የወሰዱትን ገንዘብ እስከ ቅዳሜ ተመላሽ የማያደርጉ ግለሰቦችን ከፍትህ አካላትና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመተባበር ተገቢውን የወንጀል፣ የፍትሐ ብሔርና አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ እንደሚያደርግ ባንኩ አሳስቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.