Fana: At a Speed of Life!

ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ የጤና ስርአትን ለማጠናከር አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ አረጋገጠ

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት የህፃናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) የኢትዮጵያን የጤና ስርአት ለማጠናከር አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ አረጋግጧል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ዳሬክተር ዶ/ር አቡበከር ካምፖ ጋር የጤና ስርአትን በማጠናከር ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ዶ/ር መቅደስ ዩኒሴፍ ለጤናው ዘርፍ እያደረገ የሚገኘውን ድጋፍ አድንቀው ጤና ሚኒስቴር በአጠቃላይ የጤና አገልግሎት፣ ዋሽ እና በስርአተ-ምግብ ዙሪያ ከዩኒሴፍ ጋር በትብብር ለመስራት ያለውን ዝግጁነት ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም የጤና አገልግሎት አቅርቦት ልዩነት የሚታይበት መሆኑን በመግለጽ በቀጣይ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ከዩኒሴፍ ጋር በትብብር ለመስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

የዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ዳሬክተር ዶ/ር አቡበከር ካምፖ÷ ግንዛቤ በመፍጠር፣ በመድሃኒት እና የህክምና ቁሳቁስ አቅርቦት እና በጤና ፋይናንሲንግ ዩኒሴፍ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጠል ገልጸዋል፡፡

ዩኒሴፍ የኢትዮጵያን የጤና ስርአት ለማጠናከር አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ ማረጋገጣቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ዩኒሴፍ በግጭት የተጎዱ ተቋሞችን መደገፍ፣ የጤና ባለሙያዎች ስልጠና እና የዋሽ ፕሮግራሞችን መደገፍ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን÷ ክትባት፣ የጽኑ ህሙማን ህክምና እና የህክምና ግብአቶችን በሀገር ውስጥ ማምረትን በተመለከተ በውይይቱ ላይ ተነስቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.