Fana: At a Speed of Life!

የሠራዊቱን ተጋድሎዎች ለትውልድ ለማስተላለፍ እየተሰራ ነው – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገር መከላከያ ሠራዊቱን የጀግንነት ተጋድሎዎች ለትውልድ የማስተላለፍ ሥራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለፁ።
“ስለ እናት ምድር” የተሰኘ ትኩረቱን በአገር ፍቅርና በመከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረገ ፊልም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮችና አባላት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያውያን ብዙ ታሪክ የሰሩ ቢሆንም የጀግንነት ታሪካቸውን በቅጡ አልተጻፈም ብለዋል።
ላለፉት ሁለት ዓመታት የዝግጅት ጊዜ የወሰደው “ስለ እናት ምድር” ፊልም የኢትዮጵያዊያን ታሪክ ለትውልድ ለማሻገር ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
መከላከያ ሰራዊት ታሪኩን በዚህ መንገድ ሲጽፍ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ገልጸው፤ ከዚህ በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ ሕግ ማስከበር ሂደቶችን የሚተርክ መጽሐፍ መታተሙን አስታውሰዋል።
“ስለ እናት ምድር” ፊልም የመከላከያ ሰራዊቱን የጀግንነት ተጋድሎዎች ለትውልድ የማስተላለፍ ሥራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ፊልሙ በዕውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ፣ የፊልም ዕውቀት ባላቸው ባለሙያዎችና በመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመው፤ ፊልሙ የተዘጋጀው በጦርነቱ የነበርውን ዕውነታ ለማሳየትና ታሪክን ለትውልድ ለማሻገር እንጂ ሌላ ዓላማ እንደሌለው ነው የተናገሩት።
መከላከያ ሰራዊት ለሀገር ሕልውና የመጨረሻው ምሽግ መሆኑን አስታውሰው፤ የፖለቲካ ወገንተኝነት የሌለውና ለሀገርና ለሕገ መንግሥቱ የቆመ ሰራዊት ነው ብለዋል።
ከሰራዊቱ ጋር በትብብር መሥራት ጀግንነት ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ የፊልሙን አዘጋጆችና ታሳታፊዎች አመስግነዋል።
መከላከያ ሰራዊት ወደፊትም ታሪክ እየሰራ፤ የሰራውንም ታሪክ እየጻፈ እንደሚቀጥል መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የፊልሙ አዘጋጅ አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ በበኩሉ ለእናት ሀገር ሕይወታቸውን ሳይሳሱ ለሚሰጡ የሰራዊት አባላት እንዲህ አይነት ሥራ በመሠራቱ እንደተደሰተ ገልጿል።
በቀጣይም መሰል ሥራዎችን እንደሚሰራ ገልጾ፤ ሁሉም ሰው በየተሰማራበት መስክ ስለ እናት ሀገር የሚተርኩ ሥራዎችን እንዲያበረክት ጥሪ አቅርቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.