Fana: At a Speed of Life!

የአደይ አበባ ስታዲየም የምዕራፍ ሁለት ግንባታ ሊጀመር ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2016(ኤፍ ቢ ሲ) የብሔራዊ ስታዲየም (አደይ አበባ ስታዲየም) የምዕራፍ ሁለት ቀሪ የግንባታ ስራ በቅርቡ የሚጀመር መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በታህሳስ 2008 ዓ/ም ግንባታው የተጀመረ የብሔራዊ ስታዲየም (አደይ አበባ ስታዲየም) 62 ሺህ ሰዎችን በወንበር የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን ፥ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታም መጠናቀቁ ይታወቃል።

አጠቃላይ የግንባታ አፈጻጸም 50 በመቶ መድረሱንና የሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታም ከ2012 ዓ/ም ጀምሮ ለማከናወን እቅድ ተይዞ ሲሰራ የቆየ ሲሆን ፥ የክፍያ ስርዓት ችግርና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለግንባታው መዘገየት ምክንያቶች ናቸው ተብሏል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ፋሲሊቲ ልማትና አስተዳደር መሪ ስራ አስፈጻሚ አዝመራው ግዛው እንደገለጹት ፥ የብሔራዊ ስታዲየሙን የምዕራፍ ሁለት ቀሪ ግንባታ ለመጀመር የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል።

ይሁንና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለሚያስፈልጋቸው ስራዎች በቂ ገንዘብ መግኘት አለመቻሉንም ነው የተናገሩት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በግላቸው ባደረጉት ጥረት የውጭ ምንዛሬ የሚያስፈልጋቸው የሁለተኛ ምዕራፍ ስፍራዎች ወጪ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግስት ለመሸፈን መስማማቱን ጠቅሰዋል።

ለግንባታው ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶ ውጤቱ እየተጠበቀ እንደሚገኝ ጠቅሰው ፥ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግስት የውጭ ምንዛሬ ክፍያና ተጓዳኝ ጉዳዮችን በተመለከተ ውሳኔውን ሲያሳውቅ የጨረታው ውጤት ይፋ ሆኖ ግንባታው እንደሚጀመር ነው የጠቆሙት።

ኤሌክትሮመካኒካል ስራዎችና ስታዲየሙን ጣሪያ የማልበስ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከሚጠይቁ ስራዎች መካከል መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

የውጭ ምንዛሬ የማይጠይቁና በሀገር ውስጥ ተቋራጮች መከናወን የሚችሉ ስራዎች መለየታቸውንም ተናግረዋል።

ለዚህም የጨረታ ሰነድ መዘጋጀቱንና በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ነው መሪ ስራ አስፈጻሚው የገለጹት።

የድጋፍ ሰጪ መሰረተ-ልማቶች ማጠናቀቂያ ስራዎች፣ የእግረኛ መንገዶች ግንባታና የውጫዊ ገጽታን የማሳመር ስራዎች በሀገር ውስጥ ተቋራጮች እንደሚከናወኑ ጠቅሰዋል።

ለምዕራፍ ሁለት ግንባታ የሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሬ በሚፈለገው ፍጥነት ከተለቀቀ በሀገር ውስጥ የሚከናወኑ ስራዎች ጎን ለጎን በማስኬድ ግንባታውን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱን አመልክተዋል።

በምዕራፍ አንድ የስታዲየሙ የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች መጠናቀቃቸውን አስታውሰው ፥ የምዕራፍ ሁለት ግንባታ በቅርቡ ይጀመራል ብለዋል።

የስታዲየሙ ግንባታ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) እና የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ማስተናገድ በሚችል ደረጃ እየተገነባ እንደሚገኝም ነው ያመላከቱት።

ለብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ እስካሁን ከ4 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ማስተወሳቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

የሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ ጣሪያ ማልበስ፣ ወንበር መግጠም፣ የሰው ሰራሽ ሀይቅ ግንባታ፣ ዘመናዊ የደህንነት ካሜራ መግጠም፣ ሳውንድ ሲስተም መዘርጋት፣ የፓርኪንግ ቦታዎች፣ የተጫዋቾች የመለማመጃ ሜዳ እና ሌሎች ስራዎችን በውስጡ አካቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.