Fana: At a Speed of Life!

በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መንገደኛ በማጉላላት ወንጀል የተጠረጠረችው የጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኛ ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከአሰራር ውጪ መንገደኛን በማስፈራራት፣ በመፈተሽና በማጉላላት ወንጀል የተጠረጠረችው የጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኛ ላይ ተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ተፈቀደ።

ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ ለፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ የፈቀደው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ዘርፍ መርማሪ ተጠርጠሪዋን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ በማካሄድ ተጠርጣሪዋን ፍርድ ቤት አቅርቧል።

በዚህም ተጠርጣሪ ገነት መንግስቱ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ የኮሚሽኑ የውጭ መንገደኞች ፍተሻ ዘርፍ ቡድን መሪ ሆና ስትሰራ በየካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 2 ሰዓት አካባቢ አንዲት ግለሰብን ከአሰራር ውጪ ቢሮዋ ውስጥ አስጠርታ መጠኑን ያለፈ እቃ ይዘሻል በማለት በማስፈራራትና በመፈተሽ እንድትጉላላ ማድረጓን ጠቅሶ ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው ጊዜ ቀጠሮ የሰራቸውን የምርመራ ስራዎችን ገልጿል።

ግለሰቧ ከተጠረጠረችበት ወንጀል ጋር ግንኙነት ያላቸው ማስረጃ መሰብሰቡንና ቃል መቀበሉን ጠቅሶ መርማሪ ፖሊስ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አስረድቷል።

ቀሪ የምርመራ ስራዎችን አከናውኖ ለመቅረብ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠውም ጠይቋል።

ተጠርጣሪዋ በበኩሏ ህመምተኛ መሆኗን ጠቅሳ÷ ዋስትና እንዲፈቀድላት በመጠየቅ የፖሊስን ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ሊሰጥ አይገባም በማለት ተከራክራለች።

ፖሊስ በበኩሉ ተጠርጣሪዋ በዋስ ብትወጣ ማስረጃ ልታሸሽና ምስክር ልታባብል ትችላለች በማለት የዋስትና ጥያቄዋ ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል።

የግራ ቀኙን ክርክር የተመለከተው ችሎት ፖሊስ ከጀመረው የምርመራ ስራ አንጻር ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ከግምት ውስጥ በማስገባት የተጠርጣሪዋን የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው በማለፍ ለፖሊስ የዘጠኝ ቀን ጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.