Fana: At a Speed of Life!

በቀጣዮቹ ዓመታት በፋይናንስ አገልግሎት አሰጣጥ የተሻለ ለውጥ እንደሚመጣ የብሔራዊ ባንክ አመላከተ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀጣዮቹ ዓመታት በፋይናንስ አገልግሎት አሰጣጥና በዘርፉ አሳታፊነት ላይ የተሻለ ለውጥ እንደሚመጣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ተናገሩ።

የባንኩ ገዥ ይህን የተናገሩት በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ግምገማ ላይ በተካሄደ የፓናል ውይይት ላይ ነው።

ስትራቴጂው የፋይናንስ ዘርፉን ስራዎች በማዘመንና በማሳለጥ መሰረታዊ በሆነ መንገድ መቀየሩን አብራርተዋል።

የፋይናንስ ዘርፉ በቁጠባ፣ በብድር፣ በኢንሹራንስና ኢንቨስትመንት ለሚያከናውናቸው ተግባራት የዲጂታል ፋይናንስ ስርዓት አሰራር አገልግሎትን ቀልጣፋ አድርጓል ነው ያሉት።

በተለይም በፋይናንስ ተደራሽነት፣ ክፍያ ስርዓትና አካታችነት የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል።

ለአብነትም 32 ሚሊየን የሞባይል ባንክ ተጠቃሚዎችና 42 ሚሊየን የክፍያ ካርዶች መኖራቸውን ገልጸው ባለፉት 5 ዓመታት የዲጂታል ክፍያ በ750 በመቶ እድገት ማሳየቱን መናገራውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ይህም በኢትዮጵያ በቀጣዮቹ ዓመታት የፋይናንስ ስርዓቱ አገልግሎት አሰጣጥን በማቀላጠፍና አዳዲስ የዘርፉ ተዋናዮች በማብዛትና በዘርፉ መሰረታዊ ለውጥ ይኖራል ብለዋል።

ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ በትግበራ ላይ ከሚገኘው አዋጅ በተጨማሪ በቅርቡ አዲስ የባንክ የፋይናንስ ህግ እንደሚወጣ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በአሁኑ ወቅት 14 የፊንቴክ ኩባንያዎች ፈቃድ ለማግኘት በሂደት ላይ የሚገኙ ሲሆን የውጭ ባንኮች ዘርፍን በሚቀላቀሉበት ወቅት መሰረታዊ ለውጥ እንደሚመጣ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ ከቀናት በፊት የተከሰተው ችግር አሰራርን በማሻሻል ሂደት የተከሰተ ችግር መሆኑን ጠቅሰው ብሔራዊ ባንክ የማጣራት ስራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የዲጂታል ፋይናንስ ግልጽነት በተሞላበት መንገድ የተከናወኑ የገንዘብ ዝውውሮችን መከታተል የሚያስችል በመሆኑ የሚጠፋ ገንዘብ እንደማይኖር ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.