Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የፋርማሲዩቲካልና አግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ አዋጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻዎች ናቸው – የሕንድ አምባሳደር

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የፋርማሲዩቲካልና አግሮ ፕሮሰሲንግ የኢንቨስትመንት ዘርፎች አዋጭ መዳረሻዎች መሆናቸውን በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር አኒል ኩማር ራኢ ገለፁ።

አምባሳደሩ ይህን የገለፁት ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ ጋር በኤምባሲያቸው ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው።

በውይይቱም ቀድመው የነበሩ ጠንካራ የኢንቨስትመንት፣ የሰው ሀይል አቅም ግንባታ፣ ተያያዥ ግንኙነቶችን ማጠናከር፣ አዳዲስ ኢንቨስተሮችን መሳብና ኢንቨስትመንትን ተግባራዊ ማድረግ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ፥ ኮርፖሬሽኑ ከዚህ ቀደም ከሕንድ ኤምባሲ ጋር የነበረው ጠንካራ ግንኙነት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ተጨማሪ የሕንድ ባለሃብቶች በተለይም በፋርማሲዩቲካልና በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገቡ ለማድረግ መሰራት እንዳለበት አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር አኒል ኩማር ራኢ፥በኢትዮጵያ ለፋርማሲዩቲካል ዘርፍ የተሰጠው ትኩረት ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለይም ፋርማሲዩቲካል እና አግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፎች የኢንቨስትመንት መዳረሻዎች መሆናቸውን አንስተው፥ በቀጣይ በጋራ መስራት የሚቻልባቸው ጉዳዮችን ለይቶ መንቀሳቀስ እንደሚገባ አሳውቀዋል።

ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ፓርኮችና የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በፋርማሲዩቲካልና በሌሎችም የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተሰማሩ የስራ ዕድል እና የእውቀት ሽግግር መፍጠር የቻሉ 13 ያህል ግዙፍ የሕንድ ኩባንያዎች ይገኛሉም ተብሏል፡፡

ሕንድ ከቻይና ቀጥሎ ከፍተኛ ባለሀብቶችን በኢንዱስትሪ ፓርኮች በማሰማራት በሁለተኛ ደረጃ መቀመጧን ከኮርፖሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.