Fana: At a Speed of Life!

የአንጎል እጢ ምልክቶች

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እጢ ያበጠ ነገርን ጠቅልሎ የሚይዝ አገላለፅ ሲሆን፤ ባህሪውን መሰረት በማድረግ በሁለት ይከፈላል፤ አመለኛ የሆነና ገር (አመለኛ ያልሆነ) በመባል ይታወቃሉ።

አመለኛ- በተለምዶ ካንሰር ተብሎ የሚጠቀሰው ሲሆን÷ ለዚህ የበቃው እጢ ከአንድ ሰውነት ወደ ሌላ ሰውነት መዛመትና መሰራጨት እንዲሁም በአካባቢው ባሉት የአካል ክፍሎች ላይ ወረራና ጥፋት ስለሚያደርስ ጭምር ነው።

ገር የተባለው እድገቱ ቀስ ያለና የዘገመ፣ ምንም አይነት የመዛመት እድል የሌለው አካባቢያዊ ጉዳቱም ቢሆን ቀለል ያለ በመሆኑ ‘ገራገር’ ሊባል ችሏል።

የአንጎል እጢ ሲባል አመለኛውምን ገራገሩንም ይወክላል፤ አብዛኛው የአንጎል እጢ ገራገር ምድብ ውስጥ የሚካተት ሲሆን÷ የአንጎልን እጢ ገራገርም ሆኖ ለየት የሚያደርግ ባህሪ ሊኖረው የቻለው መፈናፈኛ በሌለው ጭንቅላት ውስጥ መገኘቱ ነው።

የአንጎል እጢ መንስኤ፡- እስካሁን የአንጎል እጢ መንስኤ (አጋላጭ) ነው ተብሎ የተጠቀሰው የጨረራ መጋለጥ ብቻ ነው፡፡

የአንጎል እጢ ምልክቱ ምንድነው?

የአንጎል እጢ ምልክት የሚወሰነው እጢው በተነሳበት አንጎል ክፍል አማካኝነት ነው፤ እያንዳንዱ የአንጎል ክፍል የራሱ ስራ ስላለው፤ ለማየት ከሚውለው የአንጎል ክፍል የተነሳ እጢ እይታ ላይ ችግር ይፈጥራል።

ለመራመድ ከሚውል ላይ ከሆነ የመስነፍ ችግር፤ ለማሰብ፣ ለማገናዘብ ከሚጠቅም ክፍል ላይ ከሆነ የአስተሳሰብና ማገናዘብ እንከን ይታያል።

በአጠቃላይ የአንጎል እጢ መኖር ምልክቶች ምንድናቸው?

– የራስ ምታት/ህመም/:- ቀጣይነት ያለው የራስ ህመም ቀን ከቀን እየጨመረ የሚሔድ እና በማስነጠስ አሊያም በመሳል ጊዜ የህመም መጠኑ የሚባባስ ከሆነ።

– ማንቀጥቀጥ (የሚጥል ህመም)፦ ለመጀመሪያ ጊዜ በወጣት ወይም አዋቂ ላይ የመጣል ህመም ሲከሰት ምስለ አንጎል ያስፈልጋል፡፡

– የሰውነት መስነፍ:- ሰውነት ቀስ እያለ መስነፍ ካመጣ የእጢ ምልክት ሊሆን ይችላል።

– የእይታ መቀነስ:- በብዥታ ጀምሮ የእይታ ልኬት እየቀነሰ ማምጣት እና የባህሪ፣ የአስተሳሰብ ለውጥ መኖር፣ ወደ መጨረሻ ደረጃ የደረሰ እጢ ሲሆን÷ ተከታታይና ተደጋጋሚ ትውከት ምልክት ሆኖ ሊመጣ ይችላል፡፡

የተዘረዘሩትን ምልክቶች ከታዩ በፍጥነት ተገቢውን የህክምና ምርመራ ማድረግ እንደሚገባ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በሌላ በኩል የአንጎል እጢ ለቅድመ ማወቅ የሚደረግ ምርመራ አለመኖሩ የተገለፀ ሲሆን÷ አላስፈላጊ የጨረራ ተጋላጭነትን በማስወገድ ግን ከጨረራ ጋር ተያይዞ የሚከሰትን እጢ መከላከል ይቻላል።

የአንጎል እጢ ህክምና የሚወሰነው በእጢው ባህሪ እና በሚገኝበት ቦታ ላይ በመመስረት ነው፤ ይህ እንዳለ ሆኖ ቀዶ ህክምና፣ የጨረራ እና ፀረ-ካንሰር ህክምና ሊደረግ ይችላል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.