የኩላሊት ታማሚ በማስመሰል ጓደኛቸውን መኪና ውስጥ አስተኝተው ገንዘብ ሲሰበስቡ የተገኙ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኩላሊት ታማሚ በማስመሰል ጓደኛቸውን መኪና ውስጥ አስተኝተው ገንዘብ ሲሰበስቡ የተገኙ 10 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ።
ምንም አይነት የጤና ችግር የሌለበት ጓደኛቸውን ኩላሊቶቹ ከጥቅም ውጪ የሆኑ በማስመሰል በህክምና ሰበብ ገንዘብ ሲያሰባስቡ የነበሩት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉት በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ወረዳ 14 ልዩ ቦታው አዲስ ሰፈር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው።
ግለሰቦቹ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3- B21705 አ.አ የሆነ ሚኒባስ ተሽከርካሪን በመጠቀም ገንዘቡን ሲሰበስቡ የቆዩት የኩላሊት ታማሚ ነው ያሉትን ጓደኛቸውን መኪና ውስጥ በማስተኛት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በተያዙበት ወቅትም ከ5 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ እጃቸው ላይ መገኘቱን የጠቆመው የአዲስ አበባ ፖሊስ÷በመዲናዋ በተለያዩ አካባቢዎች ተመሳሳይ የድጋፍ ጥያቄዎች እንደሚስተዋሉ ጠቅሷል፡፡
ህብረተሰቡም መሰል የማታለል ተግባር እንደሚፈጸም ተገንዝቦ ድጋፍ በሚያደርግበት ወቅት ከህክምናው ጋር የተያያዙ አግባብነት ያላቸውን ሰነዶችን በማየትና ትክክለኛነቱን በማረጋገጥ ሊሆን እንደሚገባ ፖሊስ አስገንዝቧል፡፡