ሀሰተኛ የሰነድ ማስረጃዎችን በማዘጋጀት ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ተጠርጣሪዎች ተያዙ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀሰተኛ የሰነድ ማስረጃዎችን በማዘጋጀት ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሁለት ተጠርጣሪዎች እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ፖሊስ ገለፀ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ኢንድሪስ ኤሌክትሮኒክስ ሞባይል አክሰሰሪ እና ሳሚ ፀጉር ቤት በሚል ሽፋን ሀሰተኛ ሰነድ ሲያዘጋጁ በአዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ልዩ ቦታዉ ሀብተጊዮርጊስ ድልድይ ጀርባ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
ተጠርጣዎቹ በሞባይልና ፀጉር ቤት ሽፋን ስም ፓስፖርት፣ የፅጌሬዳ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊቲ የጤና ምርመራ፣ የህይወት ፋና የውስጥ ደዌ ክሊኒክ፣ የዛክ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊቲ ክሊኒክ የህክምና ውጤት ማስረጃ ሲያዘጋጁ እንደነበር ተመላከቷል፡፡
በተጨማሪም መታወቂያዎችን፣ የትምህርት ማስረጃዎችን፣ የውጭ ጉዞ ትኬቶችን፣ የተለያዩ ሀሰተኛ የብቃት ማረጋገጫ፣ የውርስ ቅፅ፣ ደረሰኞችን፣ የልደት ምስክር ወረቀቶችን፣ የሲኦሲ ማስረጃዎችን፣ አዲሱ ብሔራዊ መታወቂያ፣ የተለያዩ የሥራ ልምድ ማስረጃዎችን ሲያዘጋጁ እንደነበር ተገልጿል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ሀሰተኛ ሰነዶችን ለማዘጋጀት ይገለገሉባቸው የነበሩ ላፕቶፕ፣ ሀርድ ዲስክ፣ ፕሪንተሮች በንግድ ሽፋን ስም በከፈቷቸው ድርጅቶች ውስጥ ከነተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ የፌዴራል ፖሊስ ገልጿል።