Fana: At a Speed of Life!

የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮች ለፍቼ ጨምበላላ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮች የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ ፍቼ ጨምባላላ በዓልን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የሲዳማ ብሔር ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንኳን ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እጅግ በደመቀ መልክ ለሚከበረው የዘመን መለወጫ ፊቼ ጨምባላላ በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል፡፡

ለመላው የብሄሩ ተወላጆች በዓሉ የሰላም፣ የመተሳሰብ፣ የፍቅርና የአንድነት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል፡፡

በተመሳሳይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በዓሉን አስመልክቶ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት፤ የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ ‘ፍቼ ጫምባላላ’ በዓል ከሲዳማ ብሔር እና ከኢትዮጵያ ህዝብ አልፎ የዓለም ቅርስ መሆኑን አስታውሰዋል።

ልዩነቶቻችንን አክብረን ብሔራዊ አርበኝነትን ለመገንባት በጀመርነዉ እንቅስቃሴ ማንነትና ኢትዮጵያዊ አንድነት ሚዛናቸዉን ጠብቀው የሚጓዙበት አቅጣጫ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል፡፡

ብሔሮችና ብሔረሰቦች ባህላቸውን፣ ታሪካቸዉንና ቋንቋቸዉን እንዲያዳብሩ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸዉን ገልፀዋል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) በዓሉን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በዓሉ ዘመድ የሚጠያየቅበት፣ የተጣሉ የሚታረቁበት፣ ፍቅር፣ ሠላም፣ መተሳሰብ፣ አብሮነትና አንድነት በተግባር የሚገለፁበት ነው ብለዋል።

ሰዎች ፈጣሪያቸውን የሚያመሰግኑበት እንዲሁም ሀገር በቀል ዕውቀቶች፣ ውብ ባህላዊ ዕሴቶችና ትውፊቶች፣ የአከባቢ አጠባበቅ ጥበብና የሥነ-ምህዳር ዕውቀቶች ለወጣቱ ትውልድ የሚተላለፍበት እንደሆነም አመልክተዋል።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በዓሉን አስመልክቶ ባስተላለፈው የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት፤ የፍቼ ጨምበላላ በዓል ህብረብሔራዊ ለሆነችዋ ሀገራችን በየጊዜው ለሚፈትኗት ችግሮች እንደ መፍቻ ቁልፍ ሆኖ የሚያስተምር፤ ዜጎች በመለያየት ሳይሆን በአንድነት፤ በመራራቅ ሳይሆን በመቀራረብ በጋራ መበልጸግንና ማደግን የሚሰብክ ልዩ ነው ብሏል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.