Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል የአድማ ብተና የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ አባላትን አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል የአድማ ብተና የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ያጠናቀቁ የቀድሞ ልዩ ሃይል አባላት ዛሬ መመረቃቸውን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።

በብር ሸለቆ ወታደራዊ ማሰልጠኛ በሁለተኛው ዙር የአድማ ብተና የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ የክልሉ የቀድሞ ልዩ ሃይል አባላት የምረቃ ስነ-ስርዓት ተካሂዷል።

የቢሮው ሃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት÷ በክልሉ እየሰፈነ የመጣውን ሰላም በዘላቂነት አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እየተሰራ ነው።

የተሃድሶ ስልጠና ወስደው የክልሉን አድማ ብተና ፖሊስ የተቀላቀሉ አባላት ከሌሎች የፌዴራልና የክልሉ የጸጥታ ሃይሎች ጎን ተሰልፈው አሁን ለመጣው ሰላም የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ለምረቃ የበቁት ሰልጣኞች የቴክኒክ፣ የአካል ብቃት፣ የስነ-ምግባር፣ የአመለካከትና የአቅም ግንባታ ስልጠና ማግኘታቸውንም ተናግረዋል።

የተሃድሶ ሰልጣኞች ከሚሊሻ እና ከመደበኛ ፖሊስ እንዲሁም ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር በመሆን የክልሉን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ቁርጠኛ ናቸውም ነው ያሉት።

ይህም የክልሉን ሰላም በዘላቂነት በማረጋገጥ የተጀመረውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ዳር ለማድረስ እንደሚያግዝ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የክልሉ ህዝብም ለጸጥታ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ለዘላቂ ሰላም መጽናት የተለመደ ትብብሩን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.