በአዲስ አበባ 150 የኤሌክትሪክ አነስተኛ ተሽከርካሪዎች ርክክብ ተከናወነ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በየደረጃዉ ለሚገኙ ተቋማት የሚያገለግሉ 150 የኤሌክትሪክ አነስተኛ ተሽከርካሪዎች (ሚኒባስ) ርክክብ አከናወነ።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹ ከማዕከል እስከ ወረዳ ለሚገኙ ተቋማት የተሰጡ ናቸው ተብሏል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹን ያስረከቡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ለህዝብ አገልግሎት ለሚሰጡ ተቋማት ተሽከርካሪዎችን መግዛት ያስፈለገበት ምክንያት የአገልግሎትን ተደራሽ ከማድረግ አንፃር ነው ብለዋል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹ በአሮጌ ተሽከርካሪዎች ምክንያት የሚመጣውን የአየር ብክለት ለመከላከል አስተዋፅዖዋቸው ከፍተኛ መሆኑንም ጠቅሰው÷ ግዢው የአየር ብክለትን መከላከል ወጪን ለመቆጠብ ያስችላል ብለዋል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹ ግዢ ለነዳጅ፣ ለጥገና እና ሰርቪስ የሚወጣውን ወጪ የሚያስቀር ሲሆን፤ ርክክቡ ከተማ አስተዳደሩ የአየር ብክለትን ለመከላከል ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ተብሏል።
በሜሮን ሙሉጌታ