Fana: At a Speed of Life!

ቀሲስ በላይ መኮንን በተጠረጠሩበት ወንጀል ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀረቡ

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት የቀሲስ በላይ መኮንንን ጨምሮ የ3 ግለሰቦችን ጊዜ ቀጠሮ መዝገብን ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ተመልክቷል።

ቀሲስ በላይ ከአንድ ሳምንት በፊት በአፍሪካ ህብረት ቅጥር ጊቢ ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአካል ቀርበው ሀሰተኛ የክፍያ ሰነዶችን በመያዝ ለ3 ግለሰቦች እና ለአንድ የግል ድርጅት ሂሳብ 6 ሚሊየን 50 ሺህ ዶላር ለማዘዋወር ለባንኩ ጥያቄ በመቅረቡና የያዙት የክፍያ ሰነድ ሀሰተኛ መሆኑ መረጋገጡን ተከትሎ በአፍሪካ ህብረት የጥበቃ ሃይሎች ተይዘው ለፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ተላልፈው መሰጠታቸውን ተከትሎ በፍርድ ቤት በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ለ7 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ሲከናወንባቸው እንደነበር ይታወሳል።

ፍርድ ቤቱ በቀሲስ በላይ መኮንን፣ ያሬድ ፍስሃ እና ዳባ ገናና በተባሉ 3 ተጠርጣሪዎች ላይ ለምርመራ ማጣሪያ ለፖሊስ በሰጠው 7 ቀን የምርመራ ጊዜ ውስጥ የተከናወኑ ስራዎችን ተመልክቷል፡፡

መርማሪ ፖሊስ በተሰጠው የ7 ቀን ጊዜ ውስጥ የምስክሮችን ቃል መቀበሉን፣ በተጠርጣሪዎች እጅ ላይ የተገኘ ኤሌክትሮኒክስ ምርመራ እንዲደረግ ለሚመለከተው ተቋም መጠየቁን፣ የቴክኒክ ምርመራ እንዲሰጠው በደብዳቤ መጠየቁን፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ለአፍሪካ ህብረት የሰነድ ማስረጃዎች እንዲሰጠው መጠየቁን፣ ተጠርጣሪዎቹ በስማቸው የሚገኙ ሂሳቦችን ለማጣራት ማረጋገጫ እንዲሰጠው በደብዳቤ መጠየቁን፣ በወቅቱ የነበረ የካሜራ ቅጂ መጠየቁን፣ ለወንጀል ተግባር የዋለ ተሽከርካሪ ማረጋገጫ ከሚመለከተው ተቋም መጠየቁን፣ በቀሲስ በላይ ሁለት መኖሪያ ቤቶች ላይ ብርበራ ማድረጉንና በብርበራ የተገኘ የጦር መሳሪያ ህጋዊነት የማረጋገጥ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

ቀረኝ ያላቸውን ስራዎችን ማለትም ከተለያዩ ተቋማት የሰነድ ማስረጃ መሰብሰብ፣ ተጨማሪ ምስክሮችን ቃል መቀበል፣ ግብረአበሮችን ተከታትሎ መያዝ፣ ተጨማሪ ሀብት የማፍራት ተግባሮች ላይ የማጣራት ስራ መስራት እንደሚያስፈልገው እና በተቀናጀና በቡድን የተፈጸመ የወንጀል ድርጊት ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያለንን መልካም ግንኙነት ጥላሸት የሚቀባ ተግባር መሆኑን ጠቅሶ ምርመራውን በተጠናከረ መንገድ በስፋት ለማከናወን ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ገልጾ መርማሪ ፖሊስ የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል።

ተጠርጣሪው ቀሲስ በላይ መኮንንን ጨምሮ ሌሎቹም ተጠርጣሪዎች በ6 ጠበቆች ተወክለው ችሎት የቀረቡ ሲሆን÷ ጠበቆቻቸው ፖሊስ ያቀረበው ጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ምክንያቶች ደንበኞቻቸውን ተጨማሪ በእስር ለማቆየት የሚያስችል አይደለም በማለት ተከራክረዋል።

በደንበኛቸው ቀሲስ በላይ የተገኘው የጦር መሳሪያ ህጋዊ መሆኑን በመጥቀስ ሀብት ማፍራት ከተጠረጠሩበት ወንጀል ጋር ሊገናኝ አይገባም በማለት የመከራከሪያ ነጥብ አንስተዋል።

የሃይማኖት አባት መሆናቸውን፣ የልማት ስራ አስተባባሪ በመሆናቸውና ቋሚ አድራሻ እንዳላቸው በመጥቀስ ቢወጡ ከመንግስት ተቋማት የሚመጡ ማስረጃዎችን የማጥፋት አቅም የላቸውም በማለት የዋስትና መብታቸው እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ጠበቆቻቸው በማህበራዊ ሚዲያና በመገናኛ ብዙሃን የቤተሰቦቻቸውንና የሳቸውን የከበረ ስም በሚያጎድፍ መልኩ ሚዛናዊ ያልሆነ ዘገባ እየቀረበባቸው ነው የሚል አቤቱታም አቅርበዋል።

ቀሲስ በላይ በበኩላቸው÷ ወንጀል አለመፈጸማቸውን ገልጸው፤ ለሀገር እና ለፖሊስ ተባባሪ መሆናቸውን እንዲሁም ምሽት ላይ እቤቴ እየሄድኩ ጠዋት ልምጣላችሁ በማለት ፖሊስን መጠየቃቸውን ለችሎቱ አስረድተዋል።

አብረዋቸው የታሰሩት ሹፌራቸውና አጃቢያቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ምንም የወንጀል ተሳትፎ በሌለበት ሁኔታ ላይ ከኔ ጋር ተጨማሪ ጊዜ በእስር ማቆየት ተገቢ አይደለም በማለት የዋስትና መብታቸው እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።

የመርማሪ ፖሊስ በጠበቆች ለተነሱ መከራከሪያ ነጥቦች ላይ መልስ የሰጠ ሲሆን÷በዚህም ምርመራው ተጠናቋል ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም ለሚለው የጠበቆች መከራከሪያ በሚመለከት ፖሊስ ሰፊ ምርመራ ስራ እንደሚቀረው ግብረአበሮችንም የመያዝ ስራ ገና እየተሰራ መሆኑን ገልጿል።

ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ተግባሮች መኖራቸውን ጠቅሶ፤ በተደረገ ብርበራ ተጨማሪ ማስረጃ ማግኘቱንና ማስረጃውን ተከትሎ ምርመራውን እያሰፋ እንደሚያጣራ ተናግሯል።

በተጨማሪም ተጠርጣሪዎቹ ቢወጡ ማስረጃ ሊሰወር ይችላል በማለትም የዋስትና ጥያቄያቸውን ተቃውሟል።

የግራ ቀኝ ክርክሩን የተመለከተው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ተጠርጣሪው ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው በማለፍ ለፖሊስ የ8 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.