Fana: At a Speed of Life!

ማህበሩና ላሚኖ ኢንጂነሪንግ ለብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ የሚውሉ መሳሪያዎች ግዥ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር እና ላሚኖ ኢንጂነሪንግ ለብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ የሚውሉ መሳሪያዎች ግዥ ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ ባንኮች ማሕበር የቦርድ ሊቀመንበር አቤ ሳኖ እና የላሚኖ ኢንጅነሪንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ስራ አስከያጅ ቅዱስ ገብረስላሴ ተፈራርመዋል።

አቶ አቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ስምምነቱ ለሚቀጥሉት 5 ዓመታት የሚተገበር ሲሆን፥ 32 ባንኮች ከ1 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ 6 ሺህ የምዝገባ ቁሳቁሶችን መግዛት የሚያስችላቸው ነው።

በስምምነቱ መሰረት ላሚኖ ኢንጂነሪንግ የምዝገባ ቁሳቁሶችን የሚያቀርብ ሲሆን፥ ይህም በሀገሪቱ በሚገኙ 11 ሺህ የባንክ ቅርንጫፎች በመጀመሪያው ዙር 40 ሚሊየን ዜጎችን የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የላሚኖ ኢንጅነሪንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ስራ አስከያጅ ቅዱስ ገብረስላሴ በበኩላቸው÷ ቁሳቁሶችን በተባለው የጥራት ደረጃና በተቀመጠው ጊዜ ለማቅረብ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የምዝገባ ቁሳቀሶቹ በፍጥነት ተሟልተው ወደ ስራ ሲገባ የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባን ለማፋጠን ሚናው የላቀ እንደሚሆን የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዮዳሔ አርዓያስላሴ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.