በጅማ ከተማ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የደስታ መግለጫ መርሃ ግብር ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጅማ ከተማ የዓለም የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ለሆኑት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የደስታ መግለጫ መርሃ ግብር ተካሄደ።
የደስታ መግለጫ መርሃ ግብሩ በዛሬው እለት ከማለዳው ጀምሮ የማርች ባንድ እና የቡና ማፍላት ስነ ስርዓትን ጨምሮ በተለያዩ የደስታ መርሃ ግብሮች ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይም የጅማ ዞን እና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የመከላከያ ሰራዊት አባላት እንዲሁም የከተማዋ እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የጅማ ከተማና የአካባቢዋ ነዋሪዎች፥ ሽልማቱ አንድነታቸውን እንደሚያጠናክርና በመከባበርና በሠላም አብሮ የመኖር እሴታቸውን እንደሚያጎለብት ተናግረዋል።
የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ መኪዩ መሀመድና የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም ሙሉ፥ በሠላም ዘርፍ የተገኘውን ድል በኢኮኖሚና በሌሎች ዘርፎች ለመድገም የጅማ ከተማና የጅማ ዞን ነዋሪዎች ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በሙክታር ጠሃ