የጥምቀት በዓል የዓለም ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ በመመዝገቡ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ገለፀች
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጥምቀት በዓላል የዓለም ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ በመመዝገቡ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ገለፀች።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ ከማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች መካከል አንዱ ሆኖ መመዝገቡን አስመልክተው ከሰዓቱን መግለጫ ሰጥተዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በመግለጫቸው፥ “እጅግ ተወዳጁና ደማቁ የጥምቀት በዓላችን የዓለም ቅርስ ሆኖ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ስለተመዘገበ እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል።
“ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው አንዱ በየዓመቱ ጥር 11 ቀን በመላ ሀገሪቱ ዳር እስከ ዳር ከልሂቅ እስከ ደቂቅ በኅብረት፣ በአንድነት፣ በሰላም፣ በስምምነትና በፍቅር ታቦቱን አጅቦ ፈጣሪውን እግዚአብሔርን እያመሰገነ በየወንዙ፣ በየአደባባዩና በየመንገዱ በፍጹም ደስታ የሚያከብረው በዓለ ጥምቀት ክርስቶስ ነው” ብለዋል።
ይህ በዓል በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ቤተ ክርስቲያኒቷ እና መንግስት እንደሁም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ሊቃውንትና ዓበይተ ሀገር ምሁራን በአጠቃላይ ምእመናንና ምእመናን የማያቋርጥ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወቃል ሲሉም ተናግረዋል።
“በመሆኑም ይህ የዘመናት ህልም እና ጥረት በዛሬው ዕለት በእግዚአብሔር ፈቃድ እውን ሆኖ ስለተመዘገበ ለደስታችን ወሰን የለውም” ሲሉም ገልፀዋል።
“ይህ በዛሬው ዕለት የተፈጸመው ታሪካዊ ጉዳይ የቤተ ክርስቲያናችን፣ የሀገራችንና የሕዝባችን ስም በዓለም ላይ ደምቆና ጐልቶ እንዲታወቅ የሚያደርግ ነው” ያሉት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፥ እንዲሁም ሀገሪቱን በቱሪዝም ክፍለ ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንድትሆን ለሚደረገው ጥረት ከፍተኛ እገዛ ያደርጋልም ብለዋል።
“ይህም እውን ሊሆን የሚችለው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የሀገሪቱ ባህልና የቱሪዝም ተቋም እንዲሁም በየሀገሩ የሚገኙ የቤተ ክርሰቲያናችን መሪዎችና አምባሳደሮች ስለበዓሉ ታላቅነት፣ ተወዳጅነትና ዕሴት ያለማቋረጥ የማስተዋወቅ ሥራ ሲሠሩ እንደሆነ ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባልም” ነው ያሉት።
በመሆኑም የበዓለ ጥምቀት በዩኔስኮ መመዝገብ ለዚህ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ተልእኮ ዕውቅና በመስጠት ረገድ የላቀ ሚና ስላለው በዓሉን፣ ሃይማኖቱን፣ ባህሉንና ሥነ በዓሉን በማስተዋወቅ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ አክለውም ሳምንቱ ለኢትዮጵያ ታላላቅ ሥራዎችን የሠሩ ኢትዮጵያውያን ልሂቃን ሰዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና አግኝተው የተሸለሙበት መሆኑንም አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የዓለም የኖቤል ሽልማታቸውን ተቀዳጅተው ወደ መንበረ መንግሥታቸው በገቡበት ቀን የበዓለ ጥምቀት በዩኔስኮ መመዝገቡ ይፋ መሆኑ ልዩ ክሥተት እንደሚያደርገውም ገልፀዋል።
“ዕውቅና አግኝቶ የተመዘገበው የጥምቀት ክርስቶስ በዓል እናንተው የአባቶቻችሁን እምነትና ባህል፣ ሥርዐትና ታሪክ ጠብቃችሁ በየዓመቱ በምታከብሩት ውብና ሳቢ፣ ማራኪና ተወዳጅ የአከባበር ሥርዐት የተገኘ መሆኑን ተገንዝባችሁ በቀጣይነትም ከነበረው ምንም ሳይጓደል በየዓመቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ የጠበቃል” ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።