ለቀጣዩ ምርጫ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መድረክ የምርጫ ስትራቴጂ እየተዘጋጀ ነው
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 3 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ በዴሞክራሲያዊ መንገድ እና ታማኝነቱን በጠበቀ መልኩ እንዲጠናቀቅ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መድረክ የምርጫ ስትራቴጂ እየተዘጋጀ ነው።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መድረክ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ብሌን አስራት ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባድረጉት ቆይታ ምርጫውን ለመከታተል እንዲረዳ መዋቅር የመፍጠር ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ማህበራቱ በተለያዩ የስራ መስኮች በሀገሪቱ እየተሳተፉ መሆናቸውን ያነሱት ሃላፊዋ፥ በሰብዓዊ መብት ጥበቃ እንዲሁም ምርጫ እና ዴሞክራሲን ማጎልበት ላይ በጋራ መስራት የሚያስችሉ ስራዎች እየተጠናቀቁ ነው ብለዋል።
ለሲቪል ማህበራቱ አባላትም በተለያየ ጊዜ በምርጫ ሂደት ሊፈጠሩ የሚችሉ ግጭቶች እና አፈታታቸውን እንዲሁም በአጠቃላይ ሂደቱ ዙሪያ የተለያዩ ስልጠናዎች ሲሰጡም ቆይተዋል።
የማህበራቱ ተግባር ቁጥሩ ከፍ ያለ ታዛቢን በማሰማራት ምርጫውን መታዘብ ሲሆን፥ ይህም ምርጫው ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ታማኝ እንዲሆን የሚሰራውን ስራ ያግዛልም ነው ያሉት ሃላፊዋ።
ከ70 በላይ ድርጅቶች በምርጫው ሂደት በጋራ ለመስራት ፈቃደኝነታቸውን ማሳየታቸውን ጠቅሰው፥ አዲሱ የሲቪል ማህበረሰብ አዋጅ በቅርቡ ከመጽደቁ ጋር ተያይዞ ሌሎች የሚቀላቀሉ እንዳሉም አንስተዋል።
ከምርጫው ጋር ተያይዞም ቁጥራቸው የበዛ የሴት እጩዎች እንዲኖሩ መድረኩ እንደሚሰራም አስረድተዋል።
ማህበራቱ የሀገሪቱን ስፋት በሚመጥን ልክ ታዛቢዎችን ማሰማራት፤ መራጩ መብት እና ግዴታውን አውቆ በምርጫው ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀገሪቱን ሚዲያ በፍትሃዊነት እንዲጠቀሙ እና በምርጫው ሂደት የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ትኩረቱን ያደርጋልም ተብሏል።
ምርጫዉ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንደሚገባውም መድረኩ ጥሪውን አቅርቧል።
በአፈወርቅ አለሙ