Fana: At a Speed of Life!

የግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪዎች ከቀረጥ ነጻ ሆነው እንደሚገቡ ይፋ ተደረገ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 4 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) 624 አይነት የግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪዎች ከቀረጥ ነጻ ሆነው የሚገቡ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የግብርና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ ዳይሬክተሮች፣ የግል ባለሀብቶች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በዛሬው ዕለት በአዳማ ከተማ ተወያይተዋል።

በዚህ ወቅትም በአይነት 624 ያህል የግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪዎች ከቀረጽ ነጻ ተደርገው የሚገቡ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴን ይፋ አድርገዋል።

በሜካናይዜሽን መሳሪያዎች ላይ በመንግስት የተደረገው የታክስ እፎይታ አሁን ያለውን ከ10 በመቶ ያልበለጠ የግብርና ሜካናይዜሽን ተደራሽነት ከፍ የሚያደርግ መሆኑ ተመላክቷል።

ከታክስ ነጻ የተደረጉት የሜካናይዜሽን መሳሪያዎች አርሶ አደሩ የሚፈልጋቸውን ግብዓቶች በአይነት፣ በመጠንና በጥራት በማቅረብ ከእርሻ ዝግጅት እስከ ሰብል አሰባሰብ ጥቅም ላይ በማዋል የአርሶ አደሩንና የባለሃብቱን ህይወት ለመቀየር የሚያስችሉ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከመሳሪያዎቹ የግዥ ስርዓት ባሻገር ከእርሻ ዝግጅት ጀምሮ ማጨድ፣ ማጓጓዝ፣ መውቃት እና ሌሎች አገልግሎቶች አሰጣጥም ከታክስ ነጻ እንደሚሆኑ የግብርና ሚኒስቴር የግብርና ሜካናይዜሽን ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ሀብቴ ገልጸዋል።

ከታክስ ነጻ ተደርገው የሚገቡት እነዚህ ዘመናዊ መሳሪያዎች የተማረው ወጣት በግብርናው ዘርፍ እንዲሰማራ በማድረግ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ የስራ ዕድል እንዲፈጠርለት የሚያስችሉ መሆናቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.