ለስደተኞች የሚሰጠው ድጋፍ እና ምላሽ የስደተኞችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም ትርጉም ባለው ደረጃ ሊያጎለብት ይገባል-ም/ጠ/ሚ አቶ ደመቀ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 7፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ለስደተኞች የሚሰጠው ድጋፍ እና ምላሽ የስደተኞችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም ትርጉም ባለው ደረጃ ሊያጎለብት እንደሚገባው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገልፀዋል።
“ዓለምአቀፍ የስደተኞች ፎረም” ላይ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ÷ ለስደተኞች የሚደረገው ድጋፍ እና ምላሽ ትርጉም አዘል መሆን እንደሚገባው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በኩል ለስደተኞች የምትሰጠው ድጋፍ እና ምላሽ ዓለምአቀፍ የስደተኞች ስምምነት ማዕቀፍ መሰረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ለስደተኞች የተሻለ ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችሏት የሪፎርም ስራዎች እያከናወነች እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
በመሠረታዊ አገልግሎት እና በማህበራዊ ደህንነት ጥበቃ ፣ በአቅም ግንባታ ፣ በክህሎት ስልጠና እና በኢኮኖሚ ትስስር ዙሪያ ኢትዮጵያ በተግባር የሚቆጠሩ ድጋፎችን ለስደተኞች ለመስጠት መዘጋጀቷን ይፋ ማድረጋቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በዚህም ለ90 ሺህ ኢትዮጵያዊያን እና ስደተኞች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለመፍጠር እንዲሁም ለ20 ሺህ ስደተኞች እና ኢትዮጵያዊያን ጥራት እና ተቀባይነት ያለው የክህሎት ስልጠና ለመስጠት መታቀዱን ነው የተናገሩት፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጣይነት ያለው እና ገበያ ተኮር የሆነ የሀይል አቅርቦት መፍትሄን ስደተኞችን ጨምቶ ለ3 ሚሊየን ሰዎች ተደራሽ ለማድረግ መተቃዱን ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም የመንግስትን ስደተኞችን የማስተናገድ አቅም በተለይ የማህበራዊ ጥበቃን ለማጠናከር በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡