Fana: At a Speed of Life!

የብልፅግና ፓርቲ የአማራ፣ የደቡብ ክልል እና የአዲስ አበባ ከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ሲያካሂዱት የነበረውን የአመራር ስልጠና አጠናቀቁ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብልፅግና ፓርቲ የአማራ፣ የደቡብ ክልል እና የአዲስ አበባ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ለአምስት ቀናት ሲሰጡ የቆዩትን የአመራር ስልጠና ዛሬ አጠናቀቁ።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት 1ኛ ዙር የአመራር ስልጠና ዛሬ ሲጠናቀቅ የላቀ የጋራ መግባባት የተፈጠረበት እንደነበር ተገልጿል።

በመድረኩ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድርና የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ተመሥገን ጥሩነህን ጨምሮ የክልል፣ የዞንና የወረዳ መሪዎች ተሳትፈዋል።

የመሪዎችንና አባላትን አቅም መገንባት፣ ለቀጣይ ተልዕኮዎች ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማዘጋጀትና በዓላማ ደረጃም ሀገሪቱን ወደ ፊት ማሻገር የሚያስችል ፓርቲ በመገንባት ዴሞክራሲንና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ያለመው ስልጠና የተሳካ እንደነበር የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አገኘሁ ተሻገር ተናግረዋል።

የክልሉን ሰላምና ደኅንነት በማረጋገጥ የሕዝቡን የመልማት ጥያቄዎች መመለስ የመሪዎቹ ቀጣይ ሥራዎች እንደሚሆኑ መግባባት ላይ መደረሱንም ነው ያረጋገጡት።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የተጀመሩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በውጤታማነት እንዲጠናቀቁም መሪዎቹ ሕዝቡን በማስተባበር የመሪነት ሚናቸውን እንዲወጡ አቅጣጫ መቀመጡንም ተናግረዋል።

በስልጠናው ከ700 በላይ የክልል፣ የዞንና ወረዳ አመራሮች መሳተፋቸውን የአድበም ዘገባ ያመለክታል።

የብልፅግና ፓርቲ የደቡብ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በሀዋሳ ለአምስት ቀናት ሲሰጥ የቆየውን የአመራር ስልጠና ዛሬ አጠናቋል።

የደቡብ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ በማጠቃለያው ላይ እንደገለጹት፥ የመደመር ዕሳቤና የብልፅግና መሰረቶችን አመራሩ በመያዝና ወቅታዊ ሁኔታዎችን በመረዳት ፈተናዎችን መሻገር የሚያስችል አዎንታዊ አመለካከት በመያዝ መወጣት እንዳለበት አመላክተዋል።

ከመዋቅር ጋር በተያያዘ ባሉ ጉዳዮችም የህዝቦችን ግንኙነትና ወንድማማችነትን በሚያጠናክር መልኩ መሰራት ያለበት እና ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ መጠናቀቅ ያለበት ስራ እንደሆነ ተገንዝቦ ሁሉም አመራር በጋራ መንቀሳቀስ እንዳለበት አስታውቀዋል።

በብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ በልጂጌ በበኩላቸው፥ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ለማጠናከር ያለመው ስልጠና የጋራ አስተሳስብና ርዕይን በአመራሩ መካከል የሚያጎለብት መሆኑና በብልፅግና መሰረቶች ላይ ያለውን ግንዛቤም የሚያሰፋ እንደሆነ ገልፀዋል።

አቶ ተስፋዬ አክለውም፥ የመዋቅር ጥያቄ በሰለጠነ መንገድ መሄድ ያለበት መሆኑንና ጥያቄውም እየተፈታ ባለበት ሁኔታ ሰላምን በማያውክ የህዝቦችን ግንኙነትና ውንድማማችነት በማይበርዝ ሁኔታ እየተሰራ በሌሎች የልማት
አጀንዳዎች ላይ ወደኃላ ሳንል በጋራ መስራት አለብን ብለዋል።

የደቡብ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው፥ “መዳረሻችን የሆነውን የሀገራችንን ብልፅግና እያስቀደምን የምንሄድ ከሆነ ውጤታማ መሆን እንችላለን” ብለዋል።

እንዲሁም ከሀገር መንግስት ግንባታ ጀምሮ መፍታት የሚገቡ ጉዳዮች መኖራቸውን አንስተው፤ ፈተናዎችን ማለፍ የሚቻለው በጋራ በመቆም ብቻ እንደሆነ ገልፀዋል።

አሁን በክልሉ የሚታየው መስከንና ሰላማዊ ሁኔት መቀጠል ያለበትና ቀሪ የቤት ስራዎች ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ መጠናቀቅ ያለባቸው መሆኑና ሌሎች የሰላም የልማትና የኮቪድ 19 መከላከል ተግባራትን ተጠናክረው መጠቀል እንዳለባቸውም መልእክት አስተላልፈዋል።

የአቅም ግንባታ ስልጠናው በአመራሩ መካከል አንጻራዊ የሆነ የሀሳብና የተግባር ተቀራራቢነት ለመፍጠር አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩም ተመላክቷል።

ስልጠናው አመራሩ የብልጽግና ፓርቲን እሳቤዎች አና ተልዕኮዎች በተሟላ ደረጃ በመገንዘብ ፈተናዎችን በብቃት ተቋቁሞ የህዝቦችን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ አጋዥ መሆኑም ተገልጿል።

በክልል ደረጃ በተሰጠው የአመራር ስልጠና ከአምሰት መቶ በላይ የሚሆኑ ከክልል ማዕከል ከዞን ከልዩ ወረዳ ከወረዳና ከከተማ አሰተዳደር የተውጣጡ አመራሮች መሳተፋቸውን ከደቡብ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በተያያዘ ዜና ባለፉት አምስት ቀናት ሲሰጥ የነበረው የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ አመራሮች 1ኛ ዙር ስልጠና መድረክ ዛሬ ተጠናቋል።

በስልጠናው ማጠቃለያ መድረክ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ እንደገለጹት ስልጠናው አመራሩ አንድነቱን የበለጠ በማጠናከር የህዝቡን ችግር ጊዜ ሳይሰጥ ለመፍታት መረባረብ እንዳለበት አቅም ሊሆነው እንደሚችል ገልጸዋል።

ተቋማዊ አሰራርን በማጠናከር የከተማችን ሰላምና ፀጥታ አስተማማኝ እንዲሆን ህዝቡን ከጎን አሰልፎ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ያስረዱት ወይዘሮ አዳነች የህግ የበላይነትን ማስከበርና የዜጎችን ደህንነት ማስከበርምየመንግስት ዋነኛ ሀላፊነት በመሆኑ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን አመላክተዋል።

የአዲስ አበባ ብልፅግና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ አለሙ በበኩላቸው ስልጠናው ለቀጣይ ተልዕኮ ተስፋ የሚሰጥ እና አሁን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ተሻግረን የሀሳብ ስንቅ እንድንይዝ ያደረገ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ብልፅግና ሁሉም ዜጎች ሊያዳብሩት የሚገባ የጠራ አስተሳሰብ መሆኑን አስረድተው አመራሩ ያሳለፍናቸውን ፈተናዎች በመገንዘብ በቀጣይ የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን የማለፊያ ትምህርት አድርጎ ሊጠቀምባቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.