Fana: At a Speed of Life!

በከተሞች የሚስተዋለውን ሰፊ የስራ እድል ክፍተት ለመፍታት የሚያግዝ ስትሬቴጅያዊ እቅድ ተዘጋጀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በከተሞች የሚስተዋለውን ሰፊ የስራ እድል ክፍተት ለመፍታት የሚያግዝ ስትሬቴጅያዊ እቅድ መዘጋጀቱን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሸን ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በቀጣዮቹ አስርት አመታት ይተገበራል ተብሎ የሚጠበቀው የከተማ ልማት መሪ እቅድ አካል የሆነው ይህ ስትራቴጅ በከተሞች ያለውን የስራ አቅም በጥናት ለይቷል፡፡

ከፋና ብሮካስቲንግ ኮርፓሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የእቅዱ ጥናት ከፍተኛ ባለሙያና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር አማካሪ አቶ ተስፋዬ ወ/ሚካኤል ÷ በከተማ ግብርና ፣ በማምረቻ ዘርፍ እና በቱሪዝም ዘርፎች ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል ጥናት ተደርጓል ብለዋል፡፡

በአገልግሎት ፣በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጅ ፈጠራ መስክም እቅዱ የኢትዮጵያ ከተሞች የስራ እድል ለመፍጠር ትኩረት እንዲያደርጉ ያስችላል ነው የተባለው፡፡

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መስፍን አሰፋ በበኩላቸው የስራ ፈጠራ ክህሎት ስልጠና የሚሰጡ ማእከላትን በከተሞች ለመገንባት ይሰራል ብለዋል፡፡

የፋይናንስ አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት ሃገር አቀፍ የስራ እድል ፈጠራ ፈንድ በቀጣይ እንደሚቋቋም ተጠቁሟል፡፡

የከተማ ልማት መሪ እቅዱ በቅርቡ ለህዝብ ውይይት ቀርቦ ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በቀጣዩ አመት ወደ ስራ እንደሚገባም ተመልክቷል፡፡

አወል አበራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.