Fana: At a Speed of Life!

በሀገሪቱ በ345 ቡና አምራች ወረዳዎች ያረጀ ቡና ጉንደላ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሀገሪቱ የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተያዘው ዓመት በ345 ቡና አምራች ወረዳዎች ያረጀ ቡና ጉንደላ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለሥልጣኑ ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የቡና ዕደሳ ንቅናቄ የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አውግቸው ተሾመ በዚህ ወቅት እንዳሉት በሀገሪቱ ለቡና ምርትና ምርትማነት መቀነስ ችግሮች መካከል ያረጀ ቡና ማሳ በስፋት መኖር በዋናነት ይጠቀሳል።

የቡና ተክሎቹ ከእርጅና ባሻገር በበሽታና በእንክብካቤ ጉድለት የተጎዱ በመሆናቸው የሚፈለገውን ያህል ምርት ማስገኘት አልቻሉም።

በዚህም ምክንያት አርሶ አደሩ ቡናን በስፋት አምርቶ ለገበያ እንዳያቀርብ ከማድርጉም በላይ ሀገሪቱ ከዘርፉ የውጭ ምንዛሪ እንዳታገኝ እንቅፋት መፍጠሩን አስታውቀዋል።

“ችግሩን ለማቃለል ዓይነተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው በመንግስት ታምኖበት ካለፈው ዓመት ወዲህ የቡና ጉንደላ ንቅናቄ በመፍጠር ስራ ውስጥ ተገብቷል” ብለዋል።

በንቅናቄም 49 ሺህ 239 ሄክታር በመጎንደልና 25 ሺህ 731 ሄክታር በነቅሎ ተከላ ማደስ መቻሉን ጠቅሰዋል።

በተያዘው  ዓመትም  “ያረጀ ቡና እደሳ ለምርትና ምርታማነት ዕድገት” በሚል መሪ ሀሳብ ሰፊ የህዝብ ንቅናቄ ይካሄዳል።

ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ በኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉልና አማራ ክልሎች በሚካሄደው ንቅናቄ በ345 ቡና አምራች ወረዳዎች ውስጥ 84 ሺህ 618 ሄክታር ለመጎንደል ጥረት ይደረጋል።

ለስራውም ስኬት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ አቶ አውግቸው አሳስበዋል።

በሀገሪቱ ለቡና ልማት ተስማሚ የሆነ አምስት ሚሊዮን 400ሺህ ሄክታር መሬት ቢኖርም እስካሁን በቡና የተሸፈነው አንድ ሚሊዮን 800ሺህ ሄክታር ብቻ እንደሆነ ያመለከቱት ደግሞ በባለስልጣኑ የቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ኤክስቴንሽን ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ናቸው።

በልማቱም ከአምስት ሚሊዮን  በላይ አርሶ አደሮች በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙና አማካይ የቡና ምርታማነቱም በሄክታር 6 ኩንታል ተኩል እንደሆነ ገልጸዋል።

እስካሁን በምርምር የተለቀቁ 42 የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች መኖራቸውን ያመለከቱት ዳይሬክተሩ ባለፈው ዓመት ምርት  ከሚሰጠው 764 ሺህ ሄክታር መሬት  494 ሺህ ቶን መገኘቱን አስታውሰዋል።

በተለይ የቡና ምርት ተገቢውን ዋጋ ካለማግኘቱ ጋር ተያይዞ በሌሎች ሰብሎች የመሸፈን ተግዳሮት አጋጥሟል።

በቡና እደሳ ዙሪያ ያሉ ተግዳሮቶችን በመፍታት  የአምራቹን፣የንግዱን ህብረተሰብና የሀገሪቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ባለፈው ዓመት በቡና ማደሱ ተግባራት የተሳተፉ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከ77 ሺህ ለሚበልጡ አርሶ አደሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱም ተመልክቷል።

ከሲዳማ ዞን ወንሾ ወረዳ የመጡት አርሶ አደር ቀዳላ ቃባቶ በሰጡት አስተያየት ለረጅም ዘመናት በቡና ልማት ሲሳተፉ መቆየታቸውን ገልጸው አሁን ላይ በሁለት ሄክታር ይዞታቸው ለይ የሚገኘውን የቡና ምርት ለማሳደግ 100 እግር ቡና በመጎንደል እየተንከባከቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ እንዳሉት የቡና ጉንደላ ምርታማነታቸውን በሶስት እጥፍ እንዳሳደገላቸውና በዓመት ከምርቱ ሽያጭ ብቻ 30 ሺህ ብር ገቢ ያገኛሉ።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ ከፌደራልና ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ የሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፉ ነው።

ምንጭ፦ ኢዜአ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.