ጄነራል እንዳሻው ጣሰው አዲስ ከተሾሙት ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ጋር የስራ ርክክብ አደረጉ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 4 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ተሰናባቹ የቀድሞ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው አዲስ ከተሾሙት ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ጋር የስራ ርክክብ አደረጉ፡፡
በስራ ርክክብ ስነ-ሥርዓቱ ላይ ኮሚሽኑ በጀመራቸው የለውጥ ስራዎች ዙሪያ ገለፃ የተደረገ ሲሆን÷ የቀድሞው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው ለስራ መነሻ የሆኑ ሰነዶችን ለአዲሱ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል አስረክበዋል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ከዚህ ቀደምም ተቋሙ ውስጥ ሲሰሩ እንደነበር በመግለጽ እንደገና እድሉን አግኝተው ተቋሙን ለመምራት ኃላፊነት ስለተሰጣቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በቀጣይም ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አመራርና አባላት ጋር በመሆን የፌደራል ፖሊስን ኮሚሽንን ወደ ተሻለ፣ ዘመናዊ የፖሊስ አገልግሎት የሚሰጥበትና በአፍሪካ ተምሳሌት የሆነ ተቋም በማድረግ ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን መግለፃቸውን ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኮሚሽነር ጄነራሉ ከዚህ ቀደም የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የማዕከላዊ መረጃና ወንጀል ኢንተለጀንስ ይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ሀላፊ እንዲሁም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል ሆነው እስከሚሾሙ ድረስ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ያገለግሉና የካበተ የሙያ ልምድ ያላቸው የፖሊስ መኮንን መሆናቸው ይታወቃል፡፡