የአሜሪካ ሴኔት በፕሬዚዳንት ትራምፕ ላይ የተከፈተውን የክስ ሂደት በይፋ አስጀመረ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 8 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ የተከፈተውን የክስ ሂደት በይፋ አስጀመረ።
በክስ ሂደቱ የሚሳተፉና በፍርድ ሂደቱ የሚሳተፉ የምክር ቤቱ አባላትም በከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኛ ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።
በክስ ሂደቱ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የተከሰሱበት ዝርዝር ጉዳይ መነበቡም ተገልጿል።
ዛሬ በይፋ የተጀመረው ክስ ትራምፕ ፈጽመውታል በተባለው የህግ ጥሰት ከስልጣን እስከማውረድ የሚያደርስ ነው።
ይህ ተፈጻሚ ይሆን ዘንድ ግን 2/3 የምክር ቤቱ አባላት ድጋፍ ያስፈልጋል።
ትራምፕ አሜሪካ ለዩክሬን የምትሰጠውን ወታደራዊ ድጋፍ እንደ ማስፈራሪያ በመጠቀም ስልጣናቸውን አላግባብ ተጠቅመዋል በሚል ውንጀላ ቀርቦባቸዋል።
ፕሬዚዳንቱ ዩክሬን በቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የእርሳቸው ተፎካካሪ በሆኑት ጆ ባይደን እና ልጃቸው ላይ ምርምራ እንድታደርግ በሚል ድርጊቱን ፈጽመዋልም ነው የተባለው።
ከዚህ ባለፈም ተገቢ ያልሆነ ተፅዕኖ በመፍጠርና ጉዳዩን በያዘው ምክር ቤት ስራ ላይ ጫና ፈጥረዋል በሚልም ክስ ቀርቦባቸዋል።
ፕሬዚዳንቱ ግን ፈጽመዋል የተባለውን ድርጊት አስተባብለዋል፤ ውንጀላውንም ፖለቲካዊ ሴራ ሲሉ አጣጥለውታል።
የትራምፕ የክስ ሂደት በአሜሪካ ታሪክ ሶስተኛው ሲሆን፥ ከእርሳቸው ቀደም ብሎ ቢል ክሊንተን በፈረንጆቹ 19 98 እንዲሁም አንድሪው ጆንሰን በ18 68 ተከሰዋል።
ይሁን እንጅ አንዳቸውም በተከሰሱበት ጉዳይ ጥፋተኛ ተብለው ከስልጣን አልተወገዱም።
ከዚያ ይልቅ ሪቻርድ ኒክሰን በፈረንጆቹ 1974 በዋተርጌት በሚገኘው የዴሞክራቶች ብሔራዊ ኮሚቴ ቢሮ ንግግር መጥለፊያ መሳሪያዎችን ተጠቅመው ተቀናቃኞቻቸውን ለመሰለል ካደረጉት ሙከራ በኋላ ምክር ቤቱ ሙሉ ምርመራ ከመጀመሩ አስቀድሞ ስልጣን መልቀቃቸው ይታወሳል።
ምክትላቸው ፎርድም የእርሳቸውን የስልጣን ዘመን ለመጨረስ መተካታቸው ይታወሳል፤ ኒክሰን በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ በፈጸሙት “የዋተር ጌት ቅሌት” ይታወሳሉ።
ምንጭ፦ ሬውተርስ