Fana: At a Speed of Life!

የአዉሮፖ ህብረት ምርጫዉን የሚታዘቡ ባለሙያዎችን የመላክ ፍላጎት እንዳለዉ አሳውቋል- አምባሳደር ዲና

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 30 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዉሮፖ ህብረት ከዚህ ቀደም ታዛቢዎችን የመላኩን እቅድ አንደሰረዘ ያስታወቀ ቢሆንም አሁን ግን ምርጫዉን  የሚታዘቡ ባለሙያዎች የመላክ ፍላጎት እንዳለዉ ማሳወቁን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገልፀዋል።

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በዛሬ ዕለት ለዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር፣ በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ እንዲሁም በ6ኛው ብሔራዊ ምርጫ የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የተሰጠ ነው።

የ6ኛው ብሔራዊ አቀፍ ምርጫን በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ እንደሚያሳየዉ የምርጫ ሂደቱ በተሞላ መልኩ እየተካሄደ ጠቅሰው፣ ምርጫውን ለመታዘብ ጥያቄ ያቀረቡ የሀገር ዉስጥ እና አለም አቀፍ ተቋማት የምርጫዉን ለመታዘብ ዝግጅታቸዉን ማጠናቀቃቸውን መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የመታዘብ ሂደቱም ቀደም ሲል በኢትዮጵያ በኩል የተቀመጡትን ቅድመ ሁኔታዎች ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ የሚፈጸም መሆኑን  ገልጸዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያ በምክንያታዊነትና በፍትሃዊነት በጋራ የመጠቀም መብት አክብራ እየሰራች እንደሆነ ገልጸዋል።

ከአባይ ውሃ 86 ከመቶ በላይ የምታመነጭ ሀገር በቅኝ ግዛት ዘመን በተደረጉ ስምምነቶች አሁንም ኢትዮጵያን ባገለለ መልኩ የመጠቀም ተግባር ተቀባይነት የሌለዉ መሆኑን ኢትዮጵያ ስትገልጽ መቆየቷን አስታውሰዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የታችኛዉ ተፋሰስ ሀገራት በማይጎዳ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን አምባሳደር ዲና በማብራሪቸዉ ተናግረዋል።

አምባሳደር ዲና ኢትዮጵያ ከመጀመሪያው የዉሃ ሙሌት ጀምሮ መረጃ ለመለዋወጥ ያላትን ፍቃደኛነት መግለጿን ተናግረዋል።

አሁንም ሀገራቱ  ባለሙያዎችን በመሰየም የሁለተኛው ዙር የግድቡን የዉሃ ሙሌትን በተመለከተ አስፈላጊው መረጃ መለዋወጥ እንዲቻል ያላትን ፍላጎት ቀደም ሲል ለሀገራቱ በይፋ ማሳወቋን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ “ለአፍሪካዊ ችግሮች፤ አፍሪካዊ መፍትሄ” በሚለዉ መርህ በአፍሪካ ህብረት አስተባበሪነት የሶስትዮሽ ድረድሩ እንዲቀጥል ያላትን ፍላጓት በተለያየ መንገዶች እየገለጸች መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሱዳንና ግብፅ በኩል ግን ጉዳዩ አለምአቀፋዊ ይዘት እንዲኖረዉ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ኢትዮጵያ ከምትከተለዉ መርህ ዉጭ መሆኑን አመልክተዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ላይ በታዘቢነት የሚሳተፉ አካላት ሚና ማሳደግን በተመለከተም ቀደም ሲል ታዛቢዎች የድርድር ሂደቱን ከመታዘብ ውጭ ሌላ ሚና እንዳልነበራቸው ገልጸው፣ በዲሞክራቲ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሊቀ-መንበርነት በተደረገው የሶስትዮሽ ድርድር ወቅት በተደረሰው ስምምነት መሰረት ግን ታዛቢዎች አስተያየታቸውን እንዲሰጡ እንዲሁም ከተደራዳሪ ሀገራት ጋር በተናጠል ሀሳብ እንዲለዋወጡ የሚፈቅዳላቸው  ስለመሆኑ አብራርተዋል።

አክለውም ግድቡ ግንባታ ሂደት እና ሁለተኛዉ ዙር የዉሃ ሙሌት በታቀደለት ጊዜ ይከናወናል ብለዋል።

የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይን በተመለከተ የሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት ረጅም ዘመን የተሻገር መሆኑን አንስተው፣ የሀገራቱን ድንበር በተመለከተም በመሪዎች እንዲሁም በጋራ የድንበር ኮሚቴዎች ደረጃ በተለያየ ጊዜ ውይይቶች ሲያደርጉ መቆየታቸዉን አስታዉሰዋል።

ሱዳን በኢትዮጵያ በትግራይ ክልል በተከናወነው የህግ ማስከበር ዘመቻን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የኢትዮጵያ ልዑላዊ ግዛትን በመውረር የቁስ እና ሰብዓዊ ሀብት ውድመት መፈጸሟን አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው አመልክተዋል።

በሱዳን በኩል በግድቡ ዙሪያ እና በድንበር ጉዳይ የሚነሳዉ ጥያቄ የሚያመለክተዉ የሶስተኛ ወገን ፍላጎት ያለበት መሆኑን እንደሆነ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ በኩል ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየሰራች መሆኑን አስታዉቀዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.