Fana: At a Speed of Life!

የመንግሥታት ግንኙነት ሥርዓት ረቂቅ አዋጅ ዳግም እንዲታይ ተወሰነ

አዲስ አበባ፣ ጥር 14 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግሥታት ግንኙነት ሥርዓት ረቂቅ አዋጅ ዳግም እንዲፈተሽ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ የፍትህና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጠየቀ።
 
ቋሚ ኮሚቴው የመንግሥታት ግንኙነት ሥርዓት ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ትናንት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።
 
በውይይቱ ላይ ረቂቅ አዋጁ የክልል መንግሥታት ያሏቸውን ሥልጣንና ተግባራት በማይጋፋ መልኩ እንዲቀራረቡና የጋራ ዕቅድ ነድፈው እንዲንቀሳቀሱ ያስችላል ተብሏል።
 
በየእርከኑ በመግሥታትና አቻ ተቋማት መካከል በመርህ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ የትብብር ሥርዓት ለመፍጠር ያግዛልም ነው የተባለው።
 
በረቂቁ ላይ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ መስተዳድሮች እንደ ክልል መጠቀሳቸው ግን አግባብ አለመሆኑን ተወያዮቹ ገልጸዋል።
 
ይህም ረቂቁ ለክልል መንግሥታት የጎንዮሽ ግንኙነት እና የክልልና የፌደራል መንግሥት የተዋረድ ግንኙነትን እንደሚመለከት ከሚለው ጋር ይጣረሳል ብለዋል።
 
ረቂቁ ክልልና የፌደራል መንግሥትን በእኩል አተያይ የማቅረብ አዝማሚያው ግልጽነት እንደሚጎድለው ያነሱት ተወያዮቹ፥ በረቂቁ ላይ ደንብ የሚያወጣው አካል ተለይቶ አለመቀመጡም የረቂቁን ምልዑነት እንደሚያጎድለው አስረድተዋል።
 
ረቂቁ ሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ ከተደረገበት በኋላ ይፅደቅ የሚል ሃሳብ ተነስቶ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፥ ረቂቅ ሕጉ ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ጋር ሲነጻጸር ኢትዮጵያ ይህን ህግ በማርቀቅ ረገድ መዘግየቷ ተጠቁሞ ውሳኔ እንዲሰጥበት ተጠይቋል።
 
በረቂቁ መንግሥታት በሚመሰርቷቸው የመድረክ ውሳኔዎች በ3/4 ድምፅ ይጽደቅ በሚለው ላይ፥ በማይገኙ የመድረኩ አባላት ላይ ተፈጻሚነትን በተመለከተ የተቀመጠው ሃሳብ ግልጽነት ይጎድለዋል ተብሏል።
 
ከዚህ ባለፈም ረቂቁ አስገዳጅ መሆን አለመሆኑን በተመለከተ ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት የተደረገ ሲሆን፥ ረቂቁ ተሻሽሎ እንዲቀርብ ለዳግም እንዲታይ መወሰኑን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.