Fana: At a Speed of Life!

ሚኒስቴሩ ባለፉት ስድስት ወራት 127 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ ሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፉት ስድስት ወራት 125 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ 127 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን አስታወቀ።

አፈጻጸሙ የዕቅዱን 101 በመቶ ሲሆን፥ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ28 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ብልጫ እንዳለው ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።

በስድስት ወራት ከተሰበሰበው ገቢ ውስጥ 58 በመቶ ከሀገር ውስጥ ሲሆን ቀሪው ደግሞ ከጉምሩክ ገቢ የተሰበሰበ መሆኑ ተገልጿል።

የተቋሙ ሠራተኞችና አመራሮች ስራቸውን በብቃትና ተነሳሽነት መስራታቸው እንዲሁም ግብር ከፋዩ የሚጠበቅበትን ግብር በታማኝነትና በወቅቱ መክፈሉ ለዕቅዱ መሳካት አስተዋጽኦ እንደነበረውም አስረድተዋል።

ከህግ ማስከበር ጋር በተሰራ ስራም ባለፉት ስድስት ወራት ከድርጊታቸው ያልተቆጠቡና ሀሰተኛ ደረሰኝ በመጠቀም ግብይት የፈፀሙ ድርጅቶች በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጋቸውንም አንስተዋል።

በግብይት ወቅትም ደረሰኝ የማይቆርጡ ድርጅቶች ላይ ድንገተኛ ክትትል በማድረግ ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው መቀጣታቸውን ገልጸዋል።

ግብር ከፋዮቹ በወቅቱና በታማኝነት ግብራቸውን በመክፈል የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.