በጋሞ ዞን በደረሰ የመሬት ናዳ የአራት ሰዎች ህይወት አለፈ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 22 ፣ 2012 (ኤፍ. ቢ. ሲ) በደቡብ ክልል ጋሞ ዞን ጋጮ ባባ ወረዳ ልዩ ስሙ ጋፄ ቀበሌ ዛሬ በደረሰ የመሬት ናዳ የአራት ሰዎች ህይወት ማለፉን የዞኑ ፖሊስ አስታወቀ።
አደጋው የተከሰተውው በአካባቢው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ መጣሉን ተከትሎ እንደሆነ የጋሞ ዞን ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ረታ ተክሉ ተናግረዋል፡፡
በአደጋው ህይወታቸውን ካጡት በተጨማሪ ሁለት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
እንዲሁም 12 የቤት እንስሳት ሲሞቱ በ13 አባወራዎች የሚገኙ 69 የቤተሰብ አባላትም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በቀበሌው በሚገኝ ትምህርት ቤት መጠለላቸውን ፖሊስ አስታውቋል ።
በአደጋው በ30 ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝ የመኸር ሰብልም ከጥቅም ውጭ መሆኑን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።