በጉራፋርዳ ወረዳ ከተከሰተው ሁከት ጋር በተያያዘ የወረዳው አስተዳዳሪን ጨምሮ የተለያዩ ሃላፊዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ጉራፋርዳ ወረዳ በትናንትናው ዕለት ከተከሰተው ሁከት እና ብጥብጥ ጋር በተያያዘ የወረዳው አስተዳዳሪን ጨምሮ የተለያዩ የስራ ሃላፊዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በአሁኑ ወቅት የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ በክልሉ ህግን የማስከበር እና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራ በልዩ ሁኔታ መጀመሩን የክልሉ መንግስት አስታውቋል።
በተለይም በህዝቡ ውስጥ የቆዩ ቅራኔዎችን በመፍታት መግባባት ላይ የተመሠረተች ሀገርና መንግስት ለመገንባት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲደረግ መቆየቱ ተመላክቷል።
በአንፃሩ በተለያዩ ዋልታ ረገጥ አስተሳሰቦች ሰለባ በሆኑ አካላት አንቀሳቃሽነት በተለያዩ አካባቢዎች የዜጎችን ሰላማዊ እንቅስቃሴ የሚያውኩ ተግባራት ሲፈጸሙ መቆየታቸው ነው የተገለጸው።
ክልሉ የመቻቻልና የአብሮነት ተምሳሌት ሆኖ እንዲቀጥል እና የተጀመረው ለውጥ እንዳይደናቀፍ የክልሉ መንግስት መሰል ችግሮችን ለማስወገድ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።
አሁን ላይም ለህዝቡ ሰላማዊ ኑሮ አስጊ እና ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ መሪ ተዋናይ የነበሩ አካላት ላይ የክልሉ መንግስት ህጋዊ እርምጃ መውሰድ መጀመሩ ተመላክቷል።
በዚህ መሰረትም በጉራፋርዳ ወረዳ ትላንት በተከሰተው ሁከት እና ብጥብጥ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ የተለያዩ አመራሮችና ባለሙያዎች በህግ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ነው የተገለጸው።
በቁጥጥር ስር የዋሉትም አቶ ኩንዲሳ ንጉሴ የወረዳው አስተዳዳሪ፣ አቶ ሃይሉ ይግለጡ የወረዳው ድርጅት ጽህፈት ቤት ሃላፊ፣ አቶ ቢሰጥ ወርቁ የአቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት ሃላፊ፣አቶ ኦይሳ አለሙ የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ፣ አቶ እንዳልክ ደምሴ ሰላምና ጽህፈት ቤት ሃላፊ፣ አቶ ማስቲ ፎልጂ የማዘጋጃ ቤት ሃላፊ፣ አቶ አጥናፉ ግዛው የአስተዳደር ጽህፈት ቤት ሃላፊ፣አቶ ታጋይ ሳሙኤል ኮጃ የማዘጋጃ ቤት ሃላፊ እና ሌሎች ባለሙያዎች መሆናቸው ተገልጿል።
በቀጣይ በሌሎች አከባቢዎች ህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከክልሉ መንግስት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።