Fana: At a Speed of Life!

ከለውጡ በኋላ በወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩትን የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ሲባል ጉዳያቸው ታይቶ እንዲለቀቁ አቅጣጫ ተቀምጧል – ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከለውጡ በኋላ በተለያዩ አካባቢዎች በወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩትን የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ሲባል ጉዳያቸው በአግባቡ በህግ ታይቶ እንዲለቀቁ አቅጣጫ መቀመጡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትግራይ ተወላጅ የብልፅግና ፓርቲ አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል።

የትግራይ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ተወካዮች ከትግራይ ተወላጅ ወታደራዊ እና ሲቪል ባለስልጣናት እስር ጋር በተያያዘ ጥያቄ አቅረበዋል።

እነዚህ አባላት ከለውጡ በኋላ በርካታ አመራሮች ከሁሉም አካባቢዎች መታሰራቸውን በመጥቀስ፤ አብዛኞቹ ግን የትግራይ ተወላጆች መሆናቸው በህዝብ ዘንድ ቅሬታ እና የመጠቃት ስሜት እንዲፈጠር አድርጓል ብለዋል።

ታሳሪ ግለሰቦቹ ወንጀል ይስሩ ወይም አይስሩ የፍርድ ቤት ጉዳይ መሆኑ ሳይዘነጋ ለህዝብ ሰላምና መረጋጋት ሲባል ከለውጡ በኋላ የታሰሩ ዜጎች ክስ ቢቋረጥ እና ጉዳዩ የእርቅ እና የይቅር ባይነት ማሳያ ተደርጎ ቢወሰድ ሲሉ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ከኢኮኖሚ አንፃር ትግራይን በኢኮኖሚ ለመጉዳት እየተሰራ ነው የሚል አስተሳሰብ እየሰፋ እና የለውጥ ሃይሉ ፀረ ትግራይ ተደርጎ እንዲታይ በርካታ ስራ እየተሰራ በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ የትግራይ ህዝብ መሪ በመሆናቸው ማብራሪያ ተጠይቀዋል።

በሌላ በኩል በትግራይ ህዝብ ዘንድ ከፌዴራል መንግስት እና ከጎረቤት ሀገራት ጥቃት ሊመጣ ይችላል የሚል ስጋት ስለተፈጠረ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝቡ ደህንነት አንፃር ምላሽ እንዲሰጡም ነው የተጠየቁት።

በዚሁ መድረክ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬተሪያት ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው፥ ከአማራ ክልል ጋር በተያያዘ ባነሱት ጥያቄ የምንገኘው በለውጥ ወቅት በመሆኑ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የታሰሩ ዜጎች በሆደ ሰፊነት ጉዳያቸው እንዲታይ አንስተዋል።

በባህር ዳር፣ በኦሮሞ አስተዳደር ዞን እና በሌሎችም የክልሉ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች በወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ዜጎች ጉዳያቸው በህግ ታይቶ ምህረት ቢደረግ ለሀገራዊ እድገት እና መግባባት ጠቃሚ ይሆናል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በምላሻቸው፥ ከለውጡ በኋላ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተከስተው ከነበሩ ግጭቶች እና ከለውጡ በፊት ተፈፅመው ከነበሩ የሙስና ወንጀሎች ጋር ተያይዞ የታሰሩ ዜጎች ጉዳያቸው ታይቶ ለፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት ሲባል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ተገቢውን ማጣራት አድርጎ እንዲፈታ አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል።

እስረኞች በሁሉም አካባቢዎች ስለሚገኙ ወንጀለኛን ከብሄር ጋር ማገናኘት ግን በድምሩ ሀገርን ይጎዳል ነው ያሉት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

እስረኞችን የመፍታቱ ሂደትም የህግን አግባብ ተንተርሶ መከናወን እንዳለበት ነው የገለጹት።

ዜጎቹ የሚፈቱት ተጨባጭ የህግ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለመፈፀማቸው ተረጋግጦ፤ ለውጡን ለማስቀጠል እና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እንዲሁም በመንግስት ሆደ ሰፊነት እንደሆነም ነው ያስታወቁት።

በውይይቱ የትግራይ እና አማራ ክልሎች ጥያቄዎች ጎልተው ቢቀርቡም የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል በቁጥጥር ስር የዋሉ ዜጎች ጉዳያቸው ታይቶ እንዲለቀቁ አቅጣጫ መቀመጡ ተመላክቷል።

ከኢኮኖሚ አንፃር ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡትም ምላሽ፥ የበጀት ቀመር የሚቀመጠው በፌዴሬሽን ምክር ቤት ስለሆነና የፌዴራል መንግስቱ ትግራይን የመጉዳት ሀሳብ ሊኖረው ስለማይችል ትችቱ መሰረተ ቢስ መሆኑን ተናግረዋል።

በተያዘው ዓመት በትግራይ ክልል 8 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በጀት እንደተያዘ እና በዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈፀሚያ 400 ሚሊየን ብር መመደቡንም አስታውቀዋል።

ይህ በጀት በትላልቅ የክልሉ ከተሞች የሚሰሩ የውሃ ፕሮጀክቶችን፣ የመስኖ ልማት ስራዎችን፣ በፌዴራል መንግስት የሚገነቡ መንገዶችን እንዲሁም ዩኒቨርሲቲዎችን የማያካትት መሆኑንም ነው ያስረዱት።

ከሁሉም በላይ ግን በአሁኑ ወቅት ሃብት በመከፋፈል ላይ ሳይሆን ሃብት በመፍጠር ላይ ልናተኩር ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።
የሀገሪቱ በጀት ግን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መከፋፈሉ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።

ከፀጥታ አንፃር የትግራይ ህዝብ ከፌዴራል መንግስት ጥቃት ይደርስብኛል ብሎ ይሰጋል ብዬ አልገምትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህ የኮንትሮባንድ የጦር መሳሪያ ነጋዴዎች አሉባልታ ነው ብለዋል።

መንግስት በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የመከላከያ ሰራዊት እና በጀት የሚመድበው ለትግራይ ክልል እንደሆነም በመግለፅ።

በየትኛውም መንገድ የሚያሰጋ የውጭ ጥቃት በክልሉ ላይ እንደሌለም ነው ያረጋገጡት።

የትኛውንም ክልል የሚያጠቃ የውጭም ሆነ የውስጥም ሃይል የለም፤ ይህ ከሆነ ግን ጥቃቱ የኢትዮጵያ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ።
በአልአዛር ታደለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.