የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን በማረሚያ ቤቶች ለመከላከል 4 ሺህ 11 የህግ ታራሚዎች በይቅርታ እንደሚለቀቁ አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን በማረሚያ ቤቶች ለመከላከል ይቻል ዘንድ 4 ሺህ 11 የህግ ታራሚዎች በይቅርታ እንደሚለቀቁ አስታወቀ።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በጉዳዩ ላይ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እነዚህ ታራሚዎች በይቅርታ እንዲለቀቁ የይቅርታ ቦርድ ለሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት አቅርቦ ማስፀደቁን አስታውቀዋል።
የሚለቀቁት የህግ ታራሚዎች በቀላል ወንጀል እስከ ሶስት ዓመት ድረስ ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኙ፣ በማረሚያ ቤት ቆይተው የአመክሮ ጊዜያቸው እስከ አንድ ዓመት የሚቀረው፣ በግድያ ወንጀል ያልተሳተፉ የሚያጠቡ እናቶች፣ ነብሰ ጡሮች እና የውጭ ሀገር ዜጎች መካተታቸውን ነው ያመለከቱት።
በይቅርታ የሚለቀቁ የውጭ ሀገራት ዜጎችም ወደየሀገራቸው እንደሚላኩ ገልፀዋል።
በተጨማሪም የሚያጠቡ እናቶች ሆነው በእስር ላይ የሚገኙ ሰባት ሴቶች እና በሙስና ወንጀል በተባባሪነት የተሳተፉ ሴቶችም አሁን ካለው ችግር አንፃር ክሳቸው እንዲቋረጥ መደረጉን ጠቁመዋል።
እነዚህ ዜጎች ከማረሚያ ቤት ሲወጡ ተገቢው ምርመራ እንደሚደረግላቸው፣ በቫይረሱ ተጠርጣሪዎች ካሉ ወደ ለይቶ ማቆያ እንደሚሄዱ፣ ከህብረተሰቡ ጋር ሲቀላቀሉም ከወንጀል እንዲጠበቁ ዝርዝራቸው በየአካባቢው ለፖሊስ እንደሚሰጥ እና ህግ ተላልፈው ከተገኙ ይቅርታቸው ተሰርዞ በህግ እንደሚጠየቁ ወይዘሮ አዳነች ተናግረዋል።
በሀይለየሱስ መኮንን
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision