Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከቆዳና ሌጦ ማግኘት ያለባትን ያህል ጥቅም እያገኘች አይደለም ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከጥሬ ቆዳና ሌጦ ማግኘት የሚገባትን ያህል ጥቅም እያገኘች እንዳልሆነ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ የጥሬ ቆዳና ሌጦ ወጪ ንግድ ሥርዓት ተዘርግቶ ወደ ሥራ መገባቱን በሚኒስቴሩ የእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ወጪ ንግድ ግብይት ስራ ክፍል ኃላፊ አበበ ታደሰ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ከየካቲት ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአምስት ላኪዎች 62 ሺህ 846 የከብት ቆዳ ወደ ጅቡቲ፣ ናይጀሪያ እና ቶጎ ተልኮ 405 ሺህ 542 ዶላር ገቢ መገኘቱን ነው የገለጹት፡፡

የጥሬ ቆዳና ሌጦ ነጋዴዎች ለቆዳ ፋብሪካዎች የማስረከብ አቅም ቢኖራቸውም÷ የቆዳ ፋብሪካዎች ያለቀለት ምርት ለማምረት የሚያስችል መሣሪያ፣ ኬሚካል፣ የስራ ማስኬጃ ካፒታል እና ክኅሎት ዝቅተኛ መሆን ከዘርፉ በሚገኘው ገቢ ላይ ጫና ፈጥሯል ብለዋል፡፡

የቆዳ ኢንዱስትሪዎች ምርቱን በተመጣጣኝ ዋጋ መረከብ ባለመቻላቸው ከዚህ በፊት የግብይት ተሳታፊ የነበሩ የጥሬ ቆዳና ሌጦ ሰብሳቢዎችና አቅራቢዎች ከገበያ ውጭ ሆነዋል ነው ያሉት፡፡

ከሁሉም ክልሎች በርካታ የጥሬ ቆዳና ሌጦ ነጋዴዎች ከገበያ በመውጣት የንግድ ፈቃዳቸውን መመለሳቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡

በዚህም ከፍተኛ የጥሬ ቆዳና ሌጦ የምርት ብክነትና የጥራት መጓደል እያስከተለ ስለሆነ ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም አሳጥቷል ብለዋል፡፡

የጥሬ ቆዳና ሌጦ የግብይት ሂደት እና የጥራት ቁጥጥር ስራ የተቀናጀ አለመሆን፣ ባለድርሻ አካላት ለዘርፉ የሰጡት ትኩረት ማነስ ተጨማሪ ዕክሎች ስለመሆናቸውም አንስተዋል፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር መመሪያ ቁጥር 62/2012 በከፊል በተዘጋጀ ቆዳና ሌጦ (ዌት ብሉ፣ፒክልድና ክረስት ቆዳዎች) ተጥሎ የነበረው የታክስ ማስከፈያ ምጣኔ ከታኅሣሥ 2012 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ሲነሳ÷ በጥሬ ቆዳና ሌጦ የነበረው 150 በመቶ ታክስ ክፍያ ባለበት እንዲቀጥል መደረጉ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.