Fana: At a Speed of Life!

በሸገር ከተማ “የሥነ-ምህዳር አወቃቀር እንቀይራለን”በሚል ከግለሰቦች ገንዘብ የተቀበሉ ተከሳሾች እስከ 20 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሸገር ከተማ “የሥነ- ምህዳር አወቃቀር እንቀይራለን’’ በማለት በማጭበርበር ገንዘብ ከግለሰቦች የተቀበሉ ተከሳሾች እስከ 20 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ተቀጡ።

የቅጣት ውሳኔውን ያስተላለፈው የኦሮሚያ ክልል የሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍ/ቤት ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሾቹም ፥ 1ኛ ደረጄ ካሳዬ ኢፋ፣ 2ኛ አቡና አያና ገመቹ፣ 3ኛ ሹሚ መስቀል ገዳ፣ 4ኛአለማየሁ ገዛኸኝ ደምስ፣ 5ኛ ጉታ ጫካ ሁንዴ እና 6ኛ ደበላ ረጋሳ ፉፋ ናቸው።

የኦሮሚያ ፍትሕ ቢሮ የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቢ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ እና ለ እንዲሁም የሙስና ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር881/2007 አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት በሰኔ ወር 2015 ዓ.ም ተደራራቢ ክስ አቅርቦባቸዋል።

በቀረበው ክስ ላይ እንደተመላከተው ተከሳሾቹ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለራሳቸው ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ በ2014 ዓ.ም በተለያዩ ጊዜያት በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ በተለያዩ ቦታዎች የአካባቢውን ሥነ-ምህዳር አወቃቀር ለመቀየር ከባለስልጣናት እንደታዘዙ በማስመሰል ማህበር በማደራጀት ‘‘መሬት ሸንሽነን እናከፋፍላለን’’ የሚሉ ሀሰተኛ የማግባቢያ ቃላት መጠቀማቸው በክሱ ዝርዝር ላይ ተጠቅሷል።

እንደአጠቃላይ በማህበር ላደራጇቸው የተለያዩ ግለሰቦች ለእያንዳንዳቸው ‘‘200 ካሬ ሜትር ይዞታ ሸንሽነን እንሰጣለን’’ በማለት ከ4 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ ከግለሰቦች በመቀበል የመንግስት ይዞታ የሆነውን 3 ሺህ ካሬ ሜትር ይዞታ ሸንሽነው ሲያከፋፍሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጠቀሰው ዐቃቤ ሕግ የተከሳሾቹን የወንጀል ድርጊት ተሳትፎ ደረጃ በመጥቀስ ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸዋል።

ተከሳሾቹ የቀረበባቸው ክስ በችሎት እንዲደርሳቸው ከተደረገ በኃላ የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ የሰውና የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱም በክስ ዝርዝሩ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን ማረጋገጡን በመግለጽ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ቢሆንም ተከሳሾቹ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን ማስተባበል ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።

ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ የቅጣት ማክበጃ አስተያየትንና የተከሳሾቹን የቅጣት ማቅለያ አስተያየት በመያዝ 1ኛ ተከሳሽን በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።

2ኛ ተከሳሽን በሚመለከት በ16 ዓመት ከ6 ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የወሰነው ፍርድ ቤቱ ፤ ከ3ኛ እስከ 6ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾችን ደግሞ እያንዳንዳቸውን በ20 ዓመት ጽኑ እስራትና በ20 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.