Fana: At a Speed of Life!

የባህር ሃይል አባላት ከወትሮው በላቀ ደረጃ ለማንኛውም ተልዕኮ ዝግጁ መሆናቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የባህር ሃይል ሠራዊት አባላት ከወትሮው በላቀ ደረጃ ለማንኛውም ተልዕኮ ዝግጁ መሆናቸው የኢትዮጵያ ባህር ሃይል አስታውቋል፡፡

የባህር ሃይል ዋና አዛዥ ተወካይ ሬር አድሚራል ናስር አባድጋ÷ የባህር ሃይል ሠራዊት ተልዕኮውን በማንኛውም ቦታና ጊዜ እየተወጣ መሆኑን አውስተዋል፡፡

ለፀረ ሠላም ሃይሎች አፀፋዊ እርምጃ በመውሰድ የሀገርን ክብር ማፅናት ላይ ከፍተኛ ሚና እየፈፀመ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

የባህር ሃይል የሠራዊት አባላት ከወትሮው በላቀ ደረጃ ዝግጁ ናቸው ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የመከላከያ ሠራዊት ለሀገርና ለሕዝብ ሠላም ሲል ሕይወቱን የሚሰጥ ከሕዝብ ጋር አብሮ የሚኖር የሰላም ሃይል ነው ብለዋል።

ዘመኑ ከደረሰበት አዳዲስ ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎች ጋር በመላመድ ጠንካራ የባህር ሃይል መገንባት እና ከዘመኑ ጋር አብሮ መዘመን ቀጣይነት ያለው ሥራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ወታደራዊና ሳይንሳዊ እውቀትን በመጠቀም የኢትዮጵያን የውጊያ አቅም ማሳደግ የሚችል ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት በቅንጅት መስራት ይገባልም ብለዋል፡፡

የባህር ሃይል አባላት ሀገርን ከሚበትኑና ህዝብን ከሚያውኩ አሉባልታዎች ራሳቸውን በማራቅ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ሠራዊቱ የተሠጠውን ሀገራዊና ሕገ-መንግስታዊ ተልዕኮ በሰከነ መንገድ በመፈፀሙ ወገኑን ያኮራና ጠላቶቹን አንገት ያስደፋ ተግባር በመስዋዕትነቱ መፈፀሙን ጠቅሰዋል፡፡

የባሀር ሃይል አባላት የሚሰጣቸውን ማንኛውንም ግዳጅ በሚገባ ለማከናወን ራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸው ማሳሰባቸውንም የመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመላክታል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.