Fana: At a Speed of Life!

ጠንካራ የአየር ሃይል ተቋም የምንገነባው ሀገርና ህዝብ በሰላም እንዲኖር ነው – ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠንካራ አየር ሃይል የምንገነባው ሀገርና ህዝብ በሰላም እንዲኖር ነው ሲሉ የኢፌዴሪ አየር ሃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ተናገሩ።

ሌ/ጄ ይልማ ዛሬ ለከፍተኛ መኮንኖች የማዕረግ ዕድገት የማልበስ ሥነ-ሥርዓት በተካሄደበት ወቅት እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ ጠንካራ አየር ሃይል ገንብታለች።

በተያዘው በጀት ዓመት እንደ ሀገር ትልቅ ስኬት የተመዘገበበት እንደሆነ ገልጸው÷ ዓለም የደረሰበት ደረጃ ትጥቆችን ያሟላንበትና ሰፊ መሰረተ ልማት ያከናወንበት ዓመት ነው ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር የዓድዋ ድል መታሰቢያ መገንባቱ የኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰው÷ የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ጨምሮ ህዝቡ ለሀገር ልማት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያን መረጋጋት የማይወዱ ጠላቶች በየቦታው የሚፈለፍሏቸው ሃይሎች ትንኮሳ ቢያደርጉም÷ በሠራዊቱ የጀግንነት ተጋድሎ ለሀገራችን ስጋት በማይሆኑበት ደረጃ ደርሰዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ የደረሰችበትን ከፍታ በ88ኛው የአየር ሃይል የምስረታ በዓል ማሳየት መቻሉን አስታውሰው÷ ወቅቱ የሚጠይቀውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጠቁ የሰራዊቱ አባላት የተመረቁበት መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያን ውድቀት የሚናፍቁ ጠላቶች እንቅልፍ ስለማይተኙ ሰራዊቱ ሁልጊዜም ዝግጁ ነው ብለዋል።

የተቋሙ መሰረታዊ ሪፎርም በሰው ኃይል ልማት፣ በትጥቅና ቴክኖሎጂ ይበልጥ እየተጠናከረ ይቀጥላል ነው ያሉት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.