የመካከለኛው ምሥራቅ ቀጣና ችግሮች እንዲፈቱ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር ትሰራለች- ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የመካከለኛው ምሥራቅ ቀጣና ችግሮች እንዲፈቱ ከወዳጅ ሀገራትና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እንደምትሰራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።
በሰላም ዕጦት ውስጥ ያሉ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ሰላምና መረጋጋት እንዲረጋገጥም አበክራ እንደምትሰራም ገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፤ ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟንና ፍላጎቷን መሰረት ያደረገ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲን ታራምዳለች ብለዋል።
‘የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ የሀገር ሰላም፣ ልማትና ደህንነትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ነው ያነሱት።
በዚህም በተለዋዋጩ ዓለም ውስጥ ኢትዮጵያ የምትወስዳቸው አቋሞች ብሔራዊ ጥቅሟ አኳያ መዝና እንደሆነ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር ካላት መልክዓ ምድራዊና የህዝብ ለህዝብ ትስስር አኳያ የቀጣናው ቀውስና መረበሽ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ቀጥተኛ አንድምታ እንዳለው ተናግረዋል።
በዚህም የቀጣናው ችግሮች እንዲፈቱና ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሞች እንዲከበሩ ከአጋር ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እንደምትሰራ ገልፀዋል።
በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ለጎረቤት ሀገራት ቀዳሚ ትኩረት የምትሰጠው ኢትዮጵያ፤ በተለይም የጎረቤት ሀገራት ቀውስ ለሀገር እንደሚተርፍ ተናግረዋል።
በዚህም በሰላም ዕጦት ለሚቸገሩ ጎረቤት ሀገራት ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር በታሪክ የነበራትን የሰላም ማስከበር ሚና አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
ከሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ባሻገርም በቀጣናው ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል የዲፕሎማሲ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
የባሕር በርን ጨምሮ ፀጋዎችን አልምቶ በጋራ በመጠቀምና የመሰረተ ልማትና ንግድ ትስስር በማጎልበት የጋራ ዕድገትን ማረጋገጥና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።