በፋና ቴሌቪዥን ሲካሄድ የቆየው የሙዚቃ ውድድር ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በፋና ቴሌቪዥን በሚተላለፈው ፋና ላምሮት ላይ ሲካሄድ የቆየው ልዩ የሙዚቃ ውድድር በዛሬው እለት ፍፃሜውን አግኝቷል።
ለአምስት ሳምንታት በበርካታ ድምጻውያን መካከል ሲካሄድ የቆየው ውድድሩ፤ በዛሬው እለት ለፍፃሜ በደረሱ አራት ተወዳዳሪዎች መካከል ተደርጎ ነው ፍጻሜውን ያገኘው።
የፍጻሜ ውድድሩ ላይም አራት ተወዳዳሪዎች በሶስት ዙር ስራዎቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን፥ ከዳኞች እና ከተመልካች በተሰበሰበ ድምጽም የውድድሩ አሸናፊ ተለይቷል።
በዚህም መሰረት ድምጻዊ አንዱአለም ጌታቸው በውድድሩ 1ኛ በመውጣት የ100 ሺህ ብር ተሸላሚ መሆን የተቻለ ሲሆን፥ ድምጻዊ ኤልያስ ተሾመ 2ኛ በመውጣት የ75 ሺህ ብር ተሸላሚ መሆን ችሏል።
እንዲሁም ድምጻዊ መቅደስ ግርማ 3ኛ ደረጃን በመያዝ የ50 ሺህ ብር ተሸላሚ ስትሆን፥ ድምጻዊ መክብብ አሰፋ 4ኛ ደረጃን በመያዝ የ25 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆኗል።
የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ በቀለ ሙለታ በመድረኩ ላይ ተገኝተው ለውድድሩ አሸናፊዎች እና ለዝግጅቱ መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት ሽልማት እና የምስጋና የምስክር ወረቀት አበርክተዋል።
አቶ በቀለ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፥ ፋና ባለፉት 25 ዓመታት አዳዲስ ነገሮችን ይዞ በመምጣት ነው የሚታወቀው፤ ቴሌቪዥን ስርጭት ከጀመረ ሁለት ዓመታት ውስጥም በርካታ የአዳዲስ ዝግጅቶችን ይዞ ቀርቧል።
አሁን ፋና አንደኛውን ምእራፍ ጨርሶ ወደ ሁለተኛው ምእራፍ እየተሸጋገረ ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ በቀጣይ ምእራፍም ብዙ አዳዲስ ነገሮችን ይዞ ይመጣል ሲሉም ተናግረዋል።